Monday, October 27, 2014

ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለመጨመር ፈቃድ ጠየቀ

ግዙፉ የመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ፣ በሳምንት ሦስት ቀናት ከኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለማሳደግ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ፈቃድ ጠየቀ፡፡
በኳታር ኤርዌይስ የኢትዮጵያ ቀጣና ኮሜርሺያል ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አንጁም ዓሊ ሚያን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን በረራ ቢቻል በቀን ሁለት ጊዜ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ሚስተር ሚያን አየር መንገዳቸው የበረራ ቁጥር የመጨመር ፍላጐት እንዳለው ገልጸው፣ ፈቃድ እንዲሰጠው ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በቅርቡ ጥያቄውን አቅርቦ በመደራደር ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ በረራ የጀመረው በመስከረም 2005 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሳምንት ሦስት ቀናት 144 መቀመጫዎች ባሉት ኤርባስ ኤ320 አውሮፕላን ከዶሃ አዲስ አበባ ይበራል፡፡ አየር መንገዱ በረራውን የጀመረው በኢትዮጵያና በኳታር መንግሥታት በተፈረመ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የመግባቢያ ሰነድ አማካይነት ነው፡፡ ኳታር ኤርዌይስ 144 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት በመሆኑ፣ መንገደኞችን ከአዲስ አበባ ዶሃ ከወሰደ በኋላ ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት ያጓጉዛል፡፡
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ በርካታ መንገደኞች በማግኘት ላይ መሆኑን የገለጹት ሚስተር ሚያን፣ ለሁሉም አየር መንገዶች የሚበቃ ገበያ እንዳለ ጠቅሰው ከተፈቀደላቸው በቀን ሁለት ጊዜ ከዶሃ አዲስ አበባ ደርሶ መልስ በረራ ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፍላጐታችን በቀን ሁለት ጊዜ መብረር ነው፡፡ የተቻለውን ያህል እንዲፈቀድልን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር እየተደራደርን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የአቪዬሽን ባለሙያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዶሃ በረራ ባይኖረውም፣ የኳታር ኤርዌይስ ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚበር በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገበያ መሻማቱ አይቀርም ይላሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ለኳታር ኤርዌይስ የሚፈቅደው ተጨማሪ የበረራ ቁጥር ውስን ይሆናል ያሉት ባለሙያው፣ ‹‹ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ጋር ይመክራል፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 13 ያህል የውጭ አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ ይበራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሉፍታንዛ፣ ኤሚሬትስ፣ ገልፍ ኤር፣ ፍላይ ዱባይ፣ ኬንያ ኤርዌይስ፣ ኢጅፕት ኤርና ተርኪሽ ኤርላይንስ ይገኙበታል፡፡
ኳታር ኤርዌይስ እ.ኤ.አ. በ1997 በአራት አውሮፕላኖች ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የ136 አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል፡፡ ባለአምስት ኮከቡ አየር መንገድ በቅርቡ ግዙፍ የሆነውን ኤርባስ ኤ380 አውሮፕላን ተረክቧል፡፡ በተጨማሪም የቦይንግ ቢ 787 ድሪምላይነርና ቢ 777 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ አየር መንገዱ 70 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው 340 አዳዲስ አውሮፕላኖች አዟል፡፡
በአፍሪካ የገበያ አድማሱን እያሰፋ በመሆኑ በቅርቡ ከዶሃ ጂቡቲ አዲስ የበረራ መስመር እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ 
ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ በረራ የጀመረበትን አንደኛ ዓመት መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በቦራ የሕፃናት መዝናኛ ችግረኛ ሕፃናት ተማሪዎችን በማዝናናትና በመመገብ አክብሯል፡፡ ለተማሪዎቹ የመማሪያ ቁሳቁሶችንም አበርክቷል፡፡ 


‹‹ግዕዝ እንደ አንድ ቋንቋ መነጋገሪያ እስኪሆን ድረስ ወደኋላ አልልም›› መምህርት ኑኃሚን ዋቅጅራ


መምህርት ኑኃሚን ዋቅጅራ 28 ዓመቷ ሲሆን ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ መሳለሚያ አካባቢ ነው፡፡ ዕድገቷ በቤተ ክርስቲያን አካባቢ በመሆኑ ለግዕዝ ትምህርቷ መነሻ ሆኗታል፡፡
በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል ቅፅር ግቢ በቄስ ትምህርት የተጀመረው ትምህርቷ ዛሬ የግዕዝ መምህርት እንደትሆን አድርጓታል፡፡ የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት በሚሰጥበት አቡነ ጐርጐርዮስ ትምህርት ቤት ከአንደኛ እስከ 10 ክፍል የሚያገለግል የመማርያ መጻሕፍት ከዚህ ቀደም አዘጋጅታ አበርክታለች፡፡ የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ደግሞ ማንኛውም የግዕዝ ቋንቋን ማወቅ የሚፈልግ የሚማርበት ‹‹ማህቶተ ጥበብ ዘልሣነ ግዕዝ›› የመጀመሪያ ክፍል መጽሐፍ አስመርቃለች፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ግዕዝን የሚያመሰጥሩ የሚያስተምሩና እንደ እማሆይ ገላነሽ ዓይነት ሴቶች ቢኖሩም ከግዕዝ መምህርነቷ በተጨማሪ በመጽሐፍ ከትባ ለማስቀመጥ የመጀመርያዋ ሴት መሆኗን መጽሐፉ በተመረቀበት ዕለት የተገኙት የግዕዝ መምህሩ ዜና እንዳለው ተናግረዋል፡፡ መምህርት ኑኃሚን በአማርኛ እንግሊዝኛ ቋንቋ ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ዲፕሎማ፣ በሥነ መለኮት ከቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ዲፕሎማዋን አግኝታለች፡፡ በግዕዝ ሥራዎቿ ዙርያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራታለች፡፡ 
ሪፖርተር፡- ወደ ግዕዝ ትምህርት እንዴት ገባሽ?
መምህርት ኑኃሚን፡- ልጅ ሆኜ ፊደል የቆጠርኩት መሳለሚያ አማኑኤለ ቤተክርስቲያን ውስጥ በሚገኘው ቄስ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እስከ ዳዊት ድረስ እንደተማርኩ ግብረሰናይ ድርጅት መጥቶ ለችግረኛ ተማሪዎች ትምህርት ቤት አቋቋመ፡፡ አማኑኤለ ግቢ የነበርነውን የቄስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በሙሉ የመጀመርያ ተማሪ አድርጐ ተቀበለንና አንደኛ ክፍል ገባን፡፡ የመደበኛውን ትምህርት እስከ 9፡30 እየተማርን የግዕዝ ትምህርቱን የምንፈልግ በግላችን ከ9፡30 አስከ 11፡00 ሰዓት መማር ጀመርን፡፡   
ሪፖርተር፡- ግዕዝ ያስተማሯችሁ ማን ናቸው?
መምህርት ኑኃሚን፡-  በጠልሰም ሥራ የአርት ፕሮፌሰር መጋቢ ሚስጥር ጌድዮን መኰንን ናቸው፡፡ ዛሬ ለደረስኩበት የግዕዝ ዕውቀት መሠረቱን ያስያዙኝ እሳቸው ናቸው፡፡ ከሕፃንነት ጀምሮ ግዕዝ አስተምረውኛል፡፡ 11ኛ ክፍል እስክደርስ ድረስ ግዕዙን ከእሳቸው እየተማርኩ ነበር፡፡ 11ኛ ክፍል እያለሁ እሳቸው በማረፋቸው ሊቀ ህሩያን መሃሪ አስተምረውኛል፡፡ እሳቸውም ብዙም ሳይቆዩ ነው ያረፉት፡፡  
ሪፖርተር፡- ምን ያሀል ተማሪዎች ነበራችሁ?
መምህርት ኑኃሚን፡-  መደበኛ ትምህርት ላይ ብዙ ሆነን ነው የተማርነው፡፡ ግዕዙን በተጨማሪ የተማርነው ግን ጥቂት ነን፡፡ መምህራችን የሥነ ምግባር ጉዳይ ላይ ጠንካራ ናቸው፡፡ ግዕዙን ስንማር መሳሳት ያስቀጣል፡፡ ኃይለኛ ስለነበሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ማስቀረትን መርጠው ነበር፡፡ 
ሪፖርተር፡- እንዴት ልትቀጥይ ቻልሽ?
መምህርት ኑኃሚን፡- በትምህርቱ እንድገፋ ከጐኔ የነበሩት እናቴና ወንድሜ ናቸው ፡፡ ሐረር ያለው ወንድሜ የግእዝ ዕውቀት ብዙም ባይኖረውም ደብዳቤ ስጽፍለት በግዕዝና በአማርኛ እንዲሆን ያዘኝ ነበር፡፡ የፈተና ውጤት ይዤ ስገባም ቤተሰቦቼ አስቀድመው የሚያዩት የግዕዝና የሥነ ምግባር ውጤቶቼን ነበር፡፡ የግዕዝ ትምህርቴን እንድተው የአካባቢው ሰዎች እናቴን ቢወተውቷትም ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ ተገረፍኩኝ ብላ የምትቀር ከሆነ ራሷ ትወስን ነበር የምትላቸው፡፡ ሁሌም መምህር ተማሪዎቹ ውጤታማ እንዲሆኑለት ነው የሚቀጣው እኔም እንደትቀር አልፈልግም ትል ነበር፡፡ ቤተሰቦቼ ብርታት ሆነውኝ የግዕዙን ትምህርት ልቀስም ችያለሁ፡፡  
ሪፖርተር፡- ሁለቱ የግዕዝ መምህራን ካረፉ በኋላ ትምህርቱን እንዴት ቀጠላችሁ?
መምህርት ኑኃሚን፡- ግቢው ውስጥ ግእዙን እስከ 11ኛ ክፍል የተማርኩት እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ መምህራኑ በሞቱ በዓመቱ የግዕዝ መምህር ቅጥር ማስታወቂያ ወጣ፡፡ ለውድድሩ የቀረብነው እኔና ሰባት መሪ ጌታዎች ነበሩ፡፡ አንድ ሴት ሰባት ወንድ ማለት ነው፡፡ በየገጠሩ ከውሻ ጋር እየተባረሩ ግዕዝ ከተማሩ ሰዎች ጋር እንዴት ትወዳደሪያለሽ በሚል ፈተና ገጥሞኝ ነበር፡፡ ቦታውን ያገኛል ተብሎ የተጠበቀውም ከመሪ ጌታዎቹ ውስጥ ነበር፡፡ መጋቢ ሚስጥር ጌድዮን ገና ተማሪ እያለን ያሉኝን ያስታወሰኝ ወቅት ነበር፡፡ ቅኔ ማህሌት ውስጥ ሴት መግባት ስለማትችል ከዛ ልንቀስም የምንችለውን ዕውቀት ለማግኘት ፈተና ነበር፡፡ መምህራችን ‘ወንድ ብትሆኑ ስሜን ታስጠሩ ነበር’  ይሉን ነበር፡፡ አባቴን ሁሌም ሴት ልጅ ስም አታስጠራም እንዴ? እያልኩም እጠይቀው ነበር፡፡ ‘ዋቅጅራ ተብሎ የኔ ስም የሚጠራው የአንቺ አባት ስለሆንኩ አይደል’ ይለኛል፡፡ በፈተናው ወቅትም ከአካባቢዬ የገጠመኝ ፈተና ይኸው ነበር፡፡ ሆኖም ፈተናውን አልፌ በደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግዕዝ መምህርት ሆኜ በ1994 ዓ.ም. ተቀጠርኩ፡፡ ሁለት ዓመት እንዳስተማርኩ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ማንኛውም መምህር የመምህርነት ትምህርት ማስረጃ ከሌለው ማስተማር አይችልም የሚል መመርያ አወጣ፡፡ እዚያው እያስተማርኩ ቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ገብቼ በ1999 ዓ.ም. በአማርኛ፣ እንግሊዝኛ ቋንቋ ዲፕሎማ ያዝኩ፡፡ 2000 ዓ.ም. ላይ በግዕዝና በሥነ ምግባር ትምህርት ዙርያ የሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ተፅዕኖ ትፈጥራላችሁ በሚል የካቴድራሉን ትምህርት ቤት ለመገምገም ከትምህርት ቢሮ ባለሙያዎች መጡ፡፡ ሁለቱንም ትምህርት የማስተምረው እኔ ስለነበርኩ የመንፈሳዊ ሥነምግባር ትምህርት በፍላጐት ብቻ የሚሰጥ መሆኑን፣ የግዕዝ ትምህርቱ ደግሞ የወንበር ትምህርት ማለትም ውዳሴ ማርያም፣ ገድላት፣ ተአምራትን ያካተተና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ የእምነቱ ተከታዮች ብቻ የሚማሩትን ሳይሆን የግዕዙን ቋንቋ ትምህርት እንደማንኛውም አንድ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደሚማሩት አብራራሁ፡፡ የማስተምርበትን ወርሃዊና ዓመታዊ የትምህርት ዕቅድ አሳየኋቸው፡፡ ትምህርቱ ተከፋፍሎ የሚማሩበትን የኮምፒውተር ጽሑፍም አዩ፡፡ ገምጋሚዎቹ ስለግዕዝ ትምህርት የነበራቸው ግንዛቤ ከእምነቱ ጋር ብቻ የተያያዘ፡፡ ሆኖም ግዕዝ የወንበርና የቋንቋ ተብሎ የተከፈለ ተማሪዎቹም የሚማሩት የቋንቋውን ክፍል ብቻ መሆኑን አስረዳኋቸው፡፡ ከተማሪዎቹ ያገኙት መልስም ስለግዕዝ ቋንቋ ብቻ እንደሚማሩ ነበር፡፡    
ሪፖርተር፡- ካንቺ ከተረዱ በኋላ አስተያየታቸው ምን ነበር?
መምህርት ኑኃሚን፡- ስለምንሰጠው ግዕዝ ቋንቋ ትምህርት ካስረዳኋቸው በኋላ እስከምን ድረስ ትዘልቂበታለሽ ነበር ያሉኝ፡፡ የአምላክ ፈቃድ ቢሆን የግዕዝ ቋንቋ ትምህርት አገር አቀፋዊ እንዲሆን ነው የምመኘው፡፡ ግዕዝ አገር አቀፍ ቋንቋ መሆን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ አገር አቀፍ ቋንቋ ባይሆን ኖሮ በብሔራዊ ደረጃ የግዕዝ ቋንቋ ፈተና አይሰጥም ነበር፡፡ የግዕዝ ቋንቋ የተመቻቸ የትምህርት መሠረት ቢኖረው ማንኛውም ተማሪ መማር የሚችለው ነው አልኳቸው፡፡ ገምጋሚዎቹ ሀሳቤን ሲረዱ በክፍል በክፍል ከፋፍለሽ በመማርያ መጽሐፍ መልክ ብታዘጋጀው በኢትዮጵያ ደረጃ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚሁ ብትቀጥይ ጥሩ ነው አሉ፡፡ ባለሙያዎቹ አስተያየቱን ከሰጡኝ በኋላ በሒደት ከአንደኛ እስከ 10 ክፍል በየክፍሉ የተከፋፈለ የግዕዝ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት አዘጋጅቼ በማኅበረ ቅዱሳን አቡነ ጐርጐርዮስ ትምህርት ቤት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው፡፡     
ሪፖርተር፡- ማኃቶተ ጥበብ ዘልሣነ ግዕዝ አንደኛ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ያነሳሳሽ ምንድን ነው?
መምህርት ኑኃሚን፡- ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን ይዤ ነው፡፡ ደብረ ገሊላ ቅዱስ አማኑኤል ካቴድራል እያለሁ ከትምህርት ቢሮ ከመጡት ገምጋሚዎች የግዕዝ ቋንቋን በቋንቋነቱ አብዛኛው ሰው እንደማያውቀው ተረዳሁ፡፡ ስለዚህ የግዕዝ ቋንቋን ማንኛውም ሰው መማር እንደሚችል ለማሳየት በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ቋንቋውን በአደራ ተቀብላ እየተጠቀመችበት እንጂ የግሌ ነው ብላ እንዳልያዘችውና ማንኛውም ሰው እንደ አንድ ቋንቋ መማር እንደሚችል ለማሳወቅ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ግዕዝ ቋንቋን ማንኛውም ሰው መማር ይችላል፡፡ መሠረታችንም የግዕዝ ፊደል ነው፡፡ ያላወቅነው እንዴት እንደምንግባባበት ነው፡፡ ፊደል የቆጠረ ሁሉ አጠቃቀሙን ካለማወቅ እንጂ ግዕዝን ተምሯል፡፡ ሆኖም ከልጅነታችን ፊደል ቆጥረን እንጂ የግዕዝ አገባቡን ስለማናውቀው ግዕዝ ሞቷል የሚሉ አሉ፡፡ ግዕዝ እንዳልሞተ የተማርነውና እየተማርነው ያለ እንዲሁም እየተጠቀምንበት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ ግዕዝ የኢትዮጵያ ቋንቋ እንደሆነ ለማሳወቅ ነው፡፡ ሦስተኛው ያጣኋቸውን መምህሬን መጋቢ ምስጢር ጌድዮን መኰን ለማሰብ ነው፡፡    
ሪፖርተር፡- መጽሐፉን ስታዘጋጂ ያጋጠሙሽን ችግሮች ብትጠቅሽልን?
መምህርት ኑኃሚን፡- ብዙ ተቸግሬያለሁ፡፡ የመጀመርያው የግዕዝ መምህሬ ሲያስተምሩን በቃል ነው፡፡ በቃል የተማርኩትን ወደ መጽሐፍ ለመቀየር መረጃ ያስፈልገዋል፡፡ ብዙ መጻሕፍት ማየት ነበረብኝ፡፡ እስከ 900 ብር አውጥቼ የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ፅፌ ከእኔ ለተሻሉ የቤተክርስቲያን ምሁራንና አባቶች ሳስተችና ሳስገመግም ብዙዎቹ የተባበሩኝ ቢሆንም ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ መጽሐፉ እንዲታተም ለማኅበረ ቅዱሳን የገባው በ2002 ዓ.ም. ነው፡፡ የወጣው ደግሞ 2006 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ መጽሐፉን ለማሳተም ስፖንሰር ለመሆን የፈቀዱ ሰዎች ሲዲውን ለማየት ከወሰዱ በኋላ ጠፍቶባቸዋል፡፡ ከማኅበረ ቅዱሳን 2003 ዓ.ም. ለመጀመርያው እትም ተብሎ የተከፈለኝም 5 ሺሕ ብር ነው፡፡ ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያዘጋጀሁትን የግዕዝ ቋንቋ መማርያ መጻሕፍት ያለምንም ክፍያ ነው በአቡነ ጐርጐርዮስ ትምህርት ቤት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው፡፡ ማበረታቻ ተብሎ ግን 4 ሺሕ ብር ተሰጥቶኛል፡፡ ሆኖም የልፋቴን ዋጋ አላገኘሁም፡፡ የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል የግእዝ መማርያ መጽሐፍ አዘጋጅቼም ማኅበሩ እየተጠቀመበት ነው፡፡ በሌላ በኩል በምፈልገው መጠን ሕዝቡ እጅ አልደረሰም፡፡ ከዚህ አንፃር ማኅበረ ቅዱሳን ለሕዝቡ በስፋት በሚያሠራጭበትና እኔም ተጠቃሚ የምሆንበትን መንገድ እንዲያሳውቀኝ በደብዳቤ ጠይቄያለሁ፡፡ 
ሪፖርተር፡- በግዕዝ ዙርያ እስከምን ድረስ ለመሄድ አስበሻል?
መምህርት ኑኃሚን፡- ግእዝ እንደ አንድ ቋንቋ መነጋገሪያ እስኪሆን ድረስ ወደኋላ አልልም፡፡ ብዙ ነገሮቻችንን ስናይ ከግዕዝ ቋንቋ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ እኔ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ነገ የሚመጣው ትውልድ ከእኔ በተሻለ ቋንቋውን እንዲጠቀምበት እፈልጋለሁ፡፡   

ያለፈቃድ የአየር ክልል ጥሰው የገቡ አምስት የሱዳን ሔሊኮፕተሮች ታስረው ተለቀቁ

የኢትዮጵያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ጥሰው የገቡ አምስት የሱዳን ሔሊኮፕተሮችና 26 አብራሪዎቻቸው ታስረው ተለቀቁ፡፡ 
ሩሲያ ሠራሽ የሆኑት አምስት የትራንስፖርት ሔሊኮፕተሮች ንብረትነታቸው ተቀማጭነቱ ሱዳን ካርቱም የሆነ ሔሊኮፕተር አከራይ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በሱዳን ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የተመዘገበ ሆኖ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የበረራ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አብራሪዎቹ ግን ምሥራቅ አውሮፓውያን ናቸው ተብሏል፡፡
ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሦስት ሳምንት በፊት አምስቱ ሔሊኮፕተሮች የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ሳያስፈቅዱ ከካርቱም ወደ ባህር ዳር  ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ሔሊኮፕተሮቹን የተከራየው የታንዛኒያ መንግሥት ሲሆን፣ አብራሪዎቹ ዓላማቸው ከካርቱም በኢትዮጵያን አድርገው፣ ኬንያ በመቀጠል ወደ ታንዛኒያ ማቅናት ነበር፡፡ ባህር ዳር  አርፈው ነዳጅ ቀድተው ጉዟቸውን ለመቀጠል አቅደውም ነበር፡፡
ይህን ሁሉ ሲያቅዱ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የበረራ ፈቃድ (የኢትዮጵያን የአየር ክልል ለማቋረጥ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ለማረፍ) የሚሰጠውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንን አላነጋገሩም፡፡ ጉዳያችሁን አስጨርሳለሁ ያላቸውን አንድ የባህር ዳር  ነዋሪ በሰጣቸው የመተማመኛ ቃል ብቻ ይዘው፣ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአማራ ክልል በኩል ጥሰው ገብተዋል፡፡
ጉዳዩን በከፍተኛ ንቃት ሲከታተል የነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰሜን ዕዝ የአየር መቃወሚያ ክፍል፣ ሔሊኮፕተሮቹን ዒላማ ውስጥ አስገብቶ ሲቃኛቸው እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ባለሙያዎችም በአገር አቀፍ ራዳር ሲከታተሏቸው እንደነበር ታውቋል፡፡
አምስቱም ሔሊኮፕተሮች በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ባህር ዳር  ግንቦት 20 ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም አርፈዋል፡፡ ‹‹ሔሊኮፕተሮቹ የሲቪል እንደሆኑ በመታወቁ በተዋጊ ጄቶች ማጀብ አላስፈለገም፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡
ባህር ዳር  እንዳረፉ ከሔሊኮፕተሮቻቸው በቀጥታ ወደ መኪና ገብተው በኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ወደ ማረፊያ ቤት መወሰዳቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ባለሙያዎች በአብራሪዎቹ ላይ ምርመራ ማካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አብራሪዎቹ ያለፈቃድ የአንድ ሉዓላዊ አገር የአየር ክልል አልፈው በመግባታቸው የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር በሚገኘው የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
በተካሄደው ምርመራ አብራሪዎቹ ሌላ ተልዕኮ ኖሯቸው ሳይሆን በተሳሳተ አካሄድ ባህር ዳር አርፈው ነዳጅ ሞልተው ጉዟቸውን ወደ ታንዛኒያ ለመቀጠል በማቀድ ነው የሚል መተማመኛ ላይ በመደረሱ፣ ባለፈው ሳምንት አምስቱ ሔሊኮፕተሮችና 26 አብራሪዎች ተለቀው ከአገር መውጣታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
አብራሪዎቹ የተለቀቁት በዋስትና ሲሆን በቀጠሮአቸው ቀን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ የሱዳን ዲፕሎማቶች አብራሪዎቹን ለማስለቀቅ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይት መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል ምንጮች ያላቸውን ግምት ገልጸዋል፡፡
ባህር ዳር  አርፋችሁ ነዳጅ እንድትቀዱ ተፈቅዶላችኋል ብሎ ያሳሳታቸው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሔሊኮፕተሮች ነዳጅ የመያዝ አቅማቸው ውስን በመሆኑ ረዥም በረራ በሚያደርጉበት ወቅት በየቦታው በማረፍ ነዳጅ ይቀዳሉ፡፡ አንድ ሔሊኮፕተር በአማካይ በሰዓት 800 ሊትር ነዳጅ እንደሚጠቀም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ስለጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡ የሱዳን ኤምባሲን በስልክ ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በ1992 ዓ.ም. ያለፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል የገባ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አየር መከላከያ ምድብ በተተኮሰ ቮልጋ ሚሳይል ተመትቶ መጋየቱን ያስታወሱት ምንጮች፤ ‹‹የኢትዮጵያ አየር ክልል እንዲያው ዝም ብሎ ዘው ተብሎ የሚገባበት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
በዚያን ወቅት አውሮፕላኑን ያበሩ የነበሩ ሁለት የስዊድን ዜግነት ያላቸው ፓይለቶች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አውሮፕላኑ ከአሜሪካ በኪራይ የመጣ ሲሆን ወደ ሞዛምቢክ እየተጓዘ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናቱ በፊት አስመራ አርፎ ነዳጅ ቀድቶ ነበር፡፡   
፡- ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

Sunday, October 26, 2014

ከኢትዮጵያ ተረቶች














****
በረሃውን ገነት የሚያደርገው ‹‹የነፍስ ምግብ››
አንድ ሊቅ ሰው ‹‹እኔ ጠንካራ ሠራተኛ ነው አእምሮዬ ሲደነዝዝ ቴኒስ በመጫወት እደሰታለሁ ኀዘኔን ልረሳው እንድችል ያደረገኝ ግን የተዋቡ ሙዚቆችን መስማት ነው፡፡›› አለ በእርግጥም በሰውና በዓለሙ መሃከል ፍጹም ሰላም ሰጭ ሁኖ የሚያስታርቀው የዕርቅ መሥዋዕት ጣዕም ያለው ዘፈንና ሙዚቃ ቃና ነው፡፡
ውብ ድምጽ ያላቸው ወፎች በረሃ ሃገራቸው ነው፡፡ ቃና ባለው ዜማ ከተዋበ ድምፃቸው ጋራ ሲዘምሩ ግን በረሃውን ገነት ያደርጉታል፡፡ እንዳዘነም ልብ የነበረውን ምድረ በዳ የገነት ያህል ሊለውጡት ችሎታ ሲኖራቸው አዳኞች አይተዋል፡፡ እንዲሁም የላባው ውበት ሊያኮራው የሚችል የቁራ አሞራ ደግሞ በዜማውና በድምጹ ክፋት እንደገነት ያማረችውን አገር በረሃ ያደርጋታል፡፡
ሰውም በሚኖርበት ርስቱ ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የተዋጣ ቅያስ ባላቸው መንገዶች መጓዝ አይታው ሁሉ ደስ ያሰኘዋል፡፡
አበበቦችም በተተከሉበት ቦታ መጠለል አዲስ ስሜትና ዕረፍት ይሰጠዋል፡፡ ቅርፁ እጅግ አምሮ በታነፀ ቤት መኖርም ይመቸዋል፡፡ በሰገነት መቀመጥም እጅግ ክብር ያለው ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን የነፍሰን አሥራው በማንቀሳቀስ ሰውን ደስ ሊያሰኘው የሚችል ጣዕም ያለው ሙዚቃና ባህል ያለው ዘፈን ባይኖር የማንኛውም የሚታይ ውበት ሁሉ ግምቱ አባይ ይሆናል፡፡
ተመስገን ገብሬ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (ኀዳር 1935)
**********
በቆልትን በወተት
ጥራጥሬን በቆልት አድርጎ መመገቡ ጤናን ለመጠበቅ ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ በተለይም የጥቁር ሽምብራ በቆልት ለሰውነት ኃይልን ከመለገስ ባሻገር በውስጡ የሚያካብታቸው፤ አያል ቫይታሚኖች የተስተካከለ ጤናን ያጎናጽፋሉ፡፡ ገብስ ባቄላና አተርን የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች በበቆልት መልክ ተዘጋጀተው ለምግብነት ሲውሉ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል እሸት ስንዴን ወቅጦና በውኃ በጥብጦ መጠጣቱም ጤናን ያደረጃል፡፡ ለጋው የስንዴ ጭማቂ አያሌ ሻይታሚኖች አሉት፡፡ በተለይም እርጉዘ ሴት ይህን ጨማቂ አዘውትራ ከተመገበች ጤናማ ቆንጆና ብልህ ልጅ ለመውለድ እንደሚያስችላት ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ስንዴን በቆልት አድርጎ በእርጎ ወይም  ከወተት ጋር ደባልቆ መጠጣቱም ሰውነትን እንደሚያጠናክር ጠበብቱ ያስረዳሉ፡፡ ከሌሎች በቆልት ጥራጥሬዎች የስንዴው ብቅል ወደር የለሽ ጠቀሜታ አለው፡፡ እርጅናን የሚከላከለው ቫየታሚን ‹‹ኤ›› በስንዴ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡
*****
‹‹ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል››
‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡
አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡
‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡
ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡
‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡
ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …
‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡
ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡
‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡
ልጃቸው እንኳን አንድ ቀን አፏ ተስቶት ብትተቻቸው ‘አንቺም አልጋሽ የቢሮ ወንበር ነው’ ብለው ጆሮዋን ሲገርፏት እንደ ቀንድ አውጣ ተሰብስባ የሽሙጥና የኩርፊያ ልጋጓን ከመጐተት በስተቀር ቆማ አልመለሰችላቸውም፡፡ ማንንም ሰው ዝም የማሰኘት ችሎታ አላቸው፡፡
‹‹በል አንተ›› ብለው ሳይጠቁሙት ወሬ የሚጀምረውን ምሳሌ ጠቅሰው ‘መናገርን’ እስኪረግም ይወቁታል፡፡ መልካም ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ የወደቀ ምራቅ ይመልሳሉ፣ ግመል ያሰክራሉ የአንድን የሰው ፀባይ የማያልቅ የሚቃረን የሚፋቀር ጐን ይሰጡታል፡፡ ‘ድንቅነት’ በእሳቸው ምላስ ሺሕ ፊት አላት … ‘ርግማን’ እልፍ ፊት አላት፡፡
እና ስልክ ለመደወል ቢጠፉ ለአካባቢው ሆነ ለማንም አይገርምም፡፡ የሚበቃ ምክንያት አላቸው፡፡ ባይኖርም ይሰጣሉ፡፡ ከሰጡ ደግሞ መቀበል ድንቅ ነው፡፡
አበባ ሥጋውን አመቻችታ ለመቁረጥ መስመር ስትፈልግ ልስላሴውና ቅዝቃዜው ማረካት፡፡ ቁርስዋንም ስላልበላች ቁርጥ ለመሞከር የድልህ ዕቃ አውጥታ ትንሽ ድልህ መክተፊያው ጣውላ ላይ ጠብ አድርጋ እየከተፈች አልፎ አልፎ ጥሬ ሥጋ እየዋጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡ ራስ ምታቱ ግን ኦ! ኦ! ያው ነው፡፡ ሻሽዋን አጠንክራ አናቷ ዙሪያ መጠምጠሙ ነው በትንሹም ቢሆን ያዋጣት፡፡
ስልክ መደወያ ቦታው በደብሪቱ የፈጠራ ችሎታ የሚወሰን ስለሆነ፣ ጭን የመሰለ ሰውነታቸውን ተሸክመው ማድ ቤት ሲገቡ መጀመሪያ ያዩት ግራ ጐኑ ላይ ቡግንጅ ያበቀለ የመሰለውን የአበባን ፊት ነው፡፡ ይሔ ቡግንጅ ደግሞ እንደ አናሳ ፍጡር ይነቃነቃል፡፡ ደማቸው ፈላ፡፡
‹‹ለራስሽ ደገስሽው?››
ቢላውን ቀምተው ቃጡባት ‹‹አንገቷን ማለት ነው›› አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተደራሲያቸው ባይታይም፡፡ በነጠላ አይናገሩም ሲበሽቁ … የጐዳቸው አንድ ሰው ተከታይ አለው፤ እና ‹‹እናንተን ምን ማድረግ ይሻላል?›› ይላሉ … እሳቸውም ተከታይ አላቸው ግን አማራጭ ብዜቱን ገለልተኛ በግምት የሚመጠን ያደርጉታል፡፡
‹‹ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል … ሴት ደረቅ እንጀራ አነሳት? … ቢበሉት ከቂጥ በላይ አይሆን … ‘ቂጣም ያሰኛል’›› አሉ፡፡
-አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)
*******
ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን
ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡
በአርእስቱ እንደተነገረው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋተ ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡
አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.
********

ኦሞትና ጉዑር ሁለቱ ወንድማማቾች
በኦፒው አምዎንግ የተተረከ የአኙዋ ተረት
በአንድ ወቅት ኦሞትና ጉዑር የተባሉ ወንድማማቾች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ኦሞት ሚስት ሲኖረው ጉዑር ግን የለውም ነበር፡፡ ወቅቱም የአዝመራ ወቅት ስለነበረ ኦሞት ሰብሉን ከወፎች የሚጠብቅበት ማማ ላይ ሆኖ ገብሱን እየጠበቀ ሳለ ጉዑር ደግሞ ባካባቢው ሆኖ ማሳውን ይመለከት ነበር፡፡ የኦሞትም ሚስት ለሁለቱም የሚሆን ምግብ ይዛ በመምጣት ከማማው ስር አስቀመጠችላቸው፡፡
ኦሞት ቁልቁል ሲመለከት ምግቡ ከእርሱ የሚተርፍ ባይመስለውም ከማማው ላይ ወርዶ በተመለከተ ጊዜ ምግቡ ለሁለቱም እንደሚበቃ አየ፡፡ ከማማው ላይ መውጣትና መውረድ ስለሰለቸውም እዚያው እማማው ስር ቁጭ ብሎ ለወንድሙ ሳይነግረው መብላት ጀመረ፡፡
እንዲህ ብሎም አሰበ “ምግቡን ሁሉ በልቼ ስለምጨርሰው ወንድሜም ሚስቴ ምግብ እንዳመጣችልን አያውቅም፡፡”
ነገር ግን ገንፎው በጣም ብዙ ስለነበር በልቶ መጨረስ አቃተው፡፡
ስለዚህ ወንድሙን ጠርቶ “ሳልጠራህ በላሁ፡፡ አሁን ፋንታህን ብላ፡፡” አለው፡፡
ሆኖም በሁኔታው በጣም አፈረ፡፡
የዚያን እለት ምሽት ከጨለመ በኋላ አብረው ወደቤት ሲመለሱ ኦሞት ጉዑርን እንዲህ አለው “ሚስት ታገባ ዘንድ ገንዘብ እሰጥሃለሁ፡፡”
እቤትም እንደደረሱ ለወንድሙ ሚስት ያገባ ዘንድ ገንዘብ ሰጠው፡፡ አዲሲቱም ሚስት ምግብ እያመጣችላቸው ሁልጊዜ አብረው ይመገቡ ጀመር፡፡
እሱም “ምንም ነገር ብትጠይቀኝ እሰጥሃለሁ፡፡” አለው፡፡
የዚህ ተረት መልዕክትም ሁለት ሰዎች አብረው ከኖሩ የየራሳቸው ንብረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን አንደኛቸው ምንም ከሌለው እርስ በእርስ መተጋገዝና መረዳዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ያለው ለሌለው በመስጠት ሊረዳው ይገባል የሚል ነው፡፡
-ከኢትዮጵያ ተረቶች

የተመስገን ልጆች





የሸራተን አዲስ ቦልሩም አዳራሽ መድረክ ላይ በዘመነኛ ዘዬ የተሠሩ ባህላዊ አልባሳት የለበሱ ሞዴሎች ይታያሉ፡፡
የፋሽን ትዕይንት አሳይተው ከመድረኩ ከወረዱ በኋላ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ ታዳጊዎች በተርታ መድረኩ ላይ ወጡ፡፡ ታዳጊዎቹ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በጉራጊኛ፣ በትግርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች በተዜሙ ሙዚቃዎች እየታጀቡ ይወዛወዛሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከሚያዋሰኑ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዜማዎችን እየተከተሉም ይደንሱ ነበር፡፡ ከአፍሪካና ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች የመጡና በአዳራሹ የነበሩት ታዳሚዎች በተመሳሳይ ስሜት የታዳጊዎቹን ትዕይንት እያጣጣሙ ነበር፡፡
ይህን ድባብ ያስተዋልነው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በአና ጌታነህ በተዘጋጀው ‹‹አፍሪካን ሞዛይክ›› ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ የፋሽን ትዕይንት ላይ ነበር፡፡ በትዕይንቱ እኩሌታ ላይ ባህላዊ ውዝዋዜ ያቀረቡት ታዳጊዎች በ2007 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ከተካሄዱ ኮንሰርቶች አንዱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ አዲሱን ዓመት ለመቀበል በሚሌኒየም አዳራሽ የተሰባሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ቴዎድሮስ ታደሰን ተከትለው ወደ መድረክ የመጡትን ታዳጊዎች በድምቀት ነበር የተቀበሏቸው፡፡ 
በተለያዩ ብሔረሰቦች ሙዚቃዎች ያለማቋረጥ ያሳዩትን ውዝዋዜ ከቡድኑ አባላት ጥቂቱ የቆዳ ከበሮ በእጃቸው እየመቱ ያጅቡ ነበር፡፡ የተቀሩት ታዳጊዎች እጃቸውና እግራቸውን በሰንሰለት ታስረው ከሰንሰለቱ ለመውጣት እየተጣጣሩ ይደንሱ ነበር፡፡ ወደ 150 የሚጠጉት ታዳጊዎች ሰንሰለቱን ከበጠሱ በኋላም ውዝዋዜያቸውን ቀጥለዋል፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ከአንድ ብሔር ወደ ሌላው እየለወጡ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ መድረኩን ተቆጣጠሩ፡፡
ታዳሚዎቹ በጭብጨባና በጩኸት ታዳጊዎቹን እያጀቡ ነበር፡፡ ከስምንት ዓመት ልጅ ጀምሮ በቡድናቸው የሚገኘው ታዳጊዎች ‹‹የተመስገን ልጆች›› ናቸው፡፡ የተመስገን ልጆች ወደ 300 የሚጠጉ አባላት ያሉት የባህል የውዝዋዜ ቡድን ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በትልልቅ መድረኮች ላይ ለረዥም ሰዓት በሚያሳዩት ትዕይንት ታዋቂ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት መድረኮች አባላቱን በቅርብ ካየንባቸው መካከል ናቸው፡፡ የተመስገን ልጆች በሚሳተፉባቸው ዝግጅት ታዳሚዎቻቸውን በኅብረት የሚያስደምም ትዕይንት ያቀርባሉ፡፡ መድረክ ላይ ሲወዛወዙ ከፊት ለፊት የሚታዩት ሕፃን የቡድኑ አባላት የብዙዎችን ቀልብ ይገዛሉ፡፡
የተመስገን ልጆች የተሰባሰቡትና የሚሠለጥኑበት በተወዛዋዥ ተመስገን መለሰ ነው፡፡ ቡድኑ ከስምንት ዓመት በፊት በ37 አባላት ነበር የተመሠረተው፡፡ ተመስገን ወደ ውዝዋዜ የገባው ልጅ ሳለ ነበር፡፡ የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ያለ አነስተኛ ሳጥን እንደ መድረክ ተጠቅሞ ቤተሰቦቹን በእስክስታ ያዝናና ነበር፡፡ ሸማኔ አባቱና ሠዓሊ ወንድሙ ለጥበባዊ ጉዞው እገዛ እንዳረጉለት የሚናገረው ተመስገን፣ ወደ ሙያው ዘልቆ እንዲገባ መንገድ የከፈተለትን ‹‹ትንሹ ሙዚቀኛ›› ድራማ ያስታውሳል፡፡ በተወለደበት አካባቢ የተቋቋመ የቀበሌ ኪነት ቡድን አባል ስለነበር በድራማው መሳተፍ ችሏል፡፡
‹‹ትንሹ ሙዚቀኛ›› በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍለ ጊዜ የተላለፈ ድራማ ነበር፡፡ ድራማው ሙዚቃ በሚወድ የንጉሥ ልጅ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ተመስገን የንጉሡ ቧለሟል ሆኖ ይተውናል፡፡ ልዑሉ ከቤተ መንግሥት ተደብቆ ክራር ሲጫወት ቧለሟሉ እየሰለለ ለንጉሡ በመንገር ያደናቅፈዋል፡፡ ገጸ ባሕሪው በሠፈሩ ልጆች እንዲጠላ ቢያደርገውም በሥራው የተዋወቃቸው ሰዎች ወደ ለሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር መርተውታል፡፡
በወቅቱ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ስለመኖሩ እንኳን የማያውቀው ተመስገን መግቢያ ፈተና አልፎ ቴአትር ቤቱን ሲቀላቀል የ12 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ዘወትር ከትምህርት መልስ በቴአተር ቤቱ ሥልጠና ይወስዳል፡፡ በየሳምንቱ መጨረሻ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ውዝዋዜ ያቀርባሉ፡፡ በየወሩ 20 ብር እየተከፈው ለስድስት ዓመት ከሠራ በኋላ በ1995 ዓ.ም. ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ሲያቀና ዕድሜው ስላልደረሰ ከትልልቅ ተወዛዋዦች ጋር ተደርቦ እንዲሠራ ተደርገ፡፡ ከዓመታት በኋላ የቴአትር ቤቱ የውዝዋዜ ቡድን በሚያቀርባቸው ትዕይንቶች ላይ በዋነኛነት መሳተፍ ጀመረ፡፡
ተወዛዋዥ የመሆን ሕልሙ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ከዛም የሀገር ፍቅር ቡድን አባል በመሆኑ ቢሳካም ብዙ ታዳጊዎች ዕድሉን አለማግኘታቸው ያሳዝነው እንደነበረ ተመስገን ይናገራል፡፡ ሀገር ፍቅር እያለ 37 ታዳጊዎችን አሰባስቦ ማሠልጠን የጀመረውም ለታዳጊዎቹ ተስፋ ለመስጠት ነበር፡፡ የተመስገን ልጆች የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች ሲመረቁ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ በአንድ መድረክ ማቅረባቸውና ትዕይንቱ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ይቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የተመስገን ልጆች ቀስበቀስ በቁጥር ከጨመሩ በኋላ ከሙዚቃ ክሊፕ አንስቶ በተለያዩ መድረኮች ታይተዋል፡፡ የነፃነት መለሰ ‹‹ባይ ባይ›› እና የመስፍን መለሰ የጉራግኛ ሙዚቃ ክሊፖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርቡም በተካሄዱት ዓለም አቀፍ የሆቴሎች ፎረም ላይና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮን ፌዴሬሽን (ካፍ) ስብሰባ ላይ ትርዒት አቅርበዋል፡፡ ‹‹እብዶች ናችሁ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት አዘጋጅተው ያቀረቡ ሲሆን፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ፣ ጎተ፣ በኢጣልያ ባህል ማዕከል፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና በሌሎችም መድረኮች ላይ ሥራቸውን አሳይተዋል፡፡
አባላቱ ተፈትነው ቡድኑን ከተቀላቀሉ በኋላ በነፃ ይሠለጥናሉ፤ በሚጋበዙበት መድረክ ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡ ተመስገን እንደሚለው ልጆች ቀላል ከሚባል ትዕይንት ውጪ ማሳየት አይችሉም የሚል የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ ፍላጎትና ችሎታ ያላቸው ልጆች መድረክ አለማግኘታቸው በሙያው መዝለቅ እንደማይቻል ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ያለፈው የ29 ዓመት ወጣት ተመስገን ለታናናሾቹ የተሻለ መድረክ ለመስጠት ያቋቋመው ቡድን አያሌ ፈተናዎች ማለፉን ይናገራል፡፡
ልጆች ለማሠልጠን በመፈለጉ ከቤተሰቡ ጋር እስከመጋጨትና አጋዥ ማጣት ድረስ ቢያደርሰውም ቡድኑ አለመበተኑን በደስታ ተሞልቶ ይናገራል፡፡ ተመስገን እንደሚለው፣ ማንኛውም ሰው ስኬት ላይ ከመድረሱ በፊት የሚደግፈው ጥቂት ሰው ብቻ ነው፡፡ ‹‹ቤተሰብም ቢሆን አንድ ደረጃ ላይ ተደርሶ ካላየ አያበረታታም፤ አብዛኛው ወላጅ ትልቅ ደረጃ ደርሰው እስኪታይ ድረስ ልጁ ወደዚህ ጥበብ እንዲገባ አይፈልግም፤›› ይላል፡፡
የቡድኑ አባላት መድረክ ማግኘታቸው ተቀባይነት እንደሚያስገኝላቸው ያምናል፡፡ በእርግጥ ቋሚ መለማመጃ ቦታ የላቸውም፡፡ በተለይ በርካታ ተወዛዋዥ የሚያስፈልገው ትዕይነት ሲኖር ሰፊ ቦታ ተከራይተው ይለማመዳሉ፡፡ ለሙያው ያላቸው ፍቅር ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው የሚያምነው ተመስገን፣ ተወዛዋዦች እንደ ዘፈን ማጀቢያ ብቻ ሳይሆን ለብቻቸውም መሥራት እንደሚችሉ ማሳየታቸው ሁነኛ ስኬታቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ 
እንደ ተመስገን፣ ለውዝዋዜ ሙዚቃ ቢያስፈልግም ተወዛዋዦች ከሙዚቀኛ ተነጥለው ትዕይንት ማቅረብ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ሙዚቃ እያጀባቸው ውዝዋዜ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ያስረግጣል፡፡ ሌላው የተመስገን ስኬት ታዳጊዎች መሥራት የሚችሉትን ማሳየታቸው ነው፡፡ ትልልቅ መድረክ ላይ መካፈላቸው ትኩረት ያልተሰጣቸውን ታዳጊዎች የሚያበረታታ መሆኑን ይናገራል፡፡ ተመስገን ወሳኙ ዕድሜ ሳይሆን የውስጥ ፍላጎትና መሰጠት ነው ይላል፡፡
ተመስገን ከምንም በላይ በተመስገን ልጆች እንዲደሰት የሚያደርገው  ተቀባይነት ማግኘታቸው ነው፡፡ ‹‹ከተለያየ አገር ወይም ሙያ የመጡ ሰዎችን ቀልብ መግዛታችን ስኬታችን ነው፡፡ አንድ ትዕይንት ተጠናቆ ተመልካች ቆሞ ሲያጨበጭብ መመልከት በዋጋ አይተመንም፤›› ይላል፡፡
የተመስገን ልጆች ለሚጋበዙባቸው መድረኮች የተገባ የሚሉትን መልዕክት የሚያስተላልፍ ውዝዋዜ ያቀርባሉ፡፡ እንደ ምሳሌ በአፍሪካን ሞዛይክ ያሳዩት አልባሳት ላይ ያተኮረ ውዝዋዜና በካፍ ስብሰባ ወቅት ያቀረቡት እግር ኳስን የማካለ ትዕይንት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተመስገን እንደሚለው፣ በየመድረኩ ገንቢ የሚሉትን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ የ2007 ዓ.ም. የእንቁጣጣሽ ኮንሰርት ላይ እጅና እግራቸውን ታሰረው የተወዛወዙት ከድህነት፣ ከኋላቀርነት፣ ከማይምነትና ከመሳሰሉት ነፃ መውጣትን ለማሳየት ነው፡፡ እንደ ተወዛዋዦቹ ገለጻ፣ ተመልካች በየራሱ አየያይ ሊተረጉመው ቢችልም በውዝዋዜያቸው የነፃነትና ጥንካሬን ፅንሰ ሐሳብ ያስተላልፋሉ፡፡ 
በብዛት የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ላይ ቢያተኩሩም አስፈላጊ ሲሆን የተለያዩ  አገሮች ዳንስ ያቀርባሉ፡፡ ለተጠሩበት ትዕይንት አስፈላጊ ከሆነ ከድረ ገጽ ወስደው ይለማመዳሉ፡፡ አምና ክሮሺያውያን በጋበዟቸው መድረክ ላይ የክሮሺያ ባህላዊ ዳንስ አጥንተው ማቅረባቸውን ተመስገን ጠቅሷል፡፡
እስካሁን ወደ 15 የሚደርሱ የውዝዋዜ ዘዬዎችን በአንድ ትዕይንት አካተው ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ዘዬ ለማጥናት የሚሞክሩ ሲሆን፣ ሙዚቃቸውን ማግኘት የቻሉትን ብሔረሰብ ባጠቃላይ ያካትታሉ፡፡ ከስምንት ዓመት አንስቶ ያሉ ልጆችን ለረዥም ሰዓት ያለማቋርጥ መድረክ ላይ እንዲጫወቱ ለማድረግ ተከታታይ ልምምድ ማድረጋቸው ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ተመስገን ያስረዳል፡፡ እሱ እንደሚለው ሥልጠናው ወደ ቡድኑ የሚመጡ ታዳጊዎች ማንኛውንም ነገር መሥራት እንደሚችሉ ከማሳመን ይጀምራል፡፡ ‹‹ሙያውን ወደውት ስለሚሠሩ የሚሳናቸው ነገር አይኖርም፤›› የሚለው ተወዛዋዡ፣ የታዳጊዎቹ ልዩ ጥምረት ተመልካችን እንደሚማርክ ይናገራል፡፡
የቡድኑ አባላት ሥልጠና እየወሰዱና ትዕይንት እያቀረቡ በተመስገን ልጆች ክበብ ውስጥ መቆየት እስከፈለጉበት ጊዜ ይቆያሉ፡፡ ተመስገን ከቡድኑ ጎን ለጎን በቶቶት የባህል ቡድን ውስጥ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሙዚቃ ክሊፖችን ያዘጋጃል፤ የውዝዋዜ ኬሮግራፈርም ነው፡፡ ከተለያዩ ከተማዎች ለሚመጡ የባህል ቡድኖች የውዝዋዜ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በቅርብ አንድ ተወዛዋዥ የሚያልፍበት ውጣ ውረድ ላይ ትኩረት ያደረገ ‹‹መቅረዝ›› የተሰኘ ፊልም ያወጣል፡፡
መስቀል አደባባይን የመሰሉ ሰፊ ቦታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተወዛዋዦችን አቀናጅቶ ትዕይንት ማቅረብ ለወደፊት ከሚመኛቸው ውስጥ ነው፡፡ የተመስገን ልጆች በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገኝተው የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ ማስተዋወቅ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ከቅርብ ጊዜ ዕቅዳቸው አንዱ ነው፡፡
ከተመስገን ልጆች አባላት አንዱ ሀብታሙ ደረጀ የ14 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ በውዝዋዜው የቀድሞውን ወወክማ የተቀላቀለው ልጅ እያለ ነበር፡፡ ወወክማ ውስጥ ሥልጠና ከመውሰዱ በተጨማሪ የድምፃዊ ወንድሙ ተወዛዋዥ ጓደኞች ውዝዋዜ ያስተምሩት ነበር፡፡ ወደ ተመስገን ልጆች ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መድረክ ላይ የተወዛወዘበትን የአፍሪካን ሞዛይክ ዝግጅት ያስታውሳል፡፡
ቀጥሎ በሸራተን አዲስና በትዝታ ፌስቲቫል ላይ ያቀረባቸው ውዝዋዜዎችን በሐሴት ተሞልቶ ያወሳል፡፡ በተለይም የጎጃምና ጉራግኛ ውዝዋዜ የሚወደው ሀብታሙ፣ ትምህርት ጨርሶ የሙሉ ጊዜ ተወዛዋዥ የሚሆንበትን ቀን በጉጉት እንደሚጠባበቅ ይናገራል፡፡
ሌላዋ የቡድኑ አባል ኤደን ተኮላ ውዝዋዜ የጀመረችው አዲስ ቤዛ በተሰኘ ቡድን ውስጥ ነበር፡፡ የተመስገን ልጆችን ከተቀላቀለች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ በቡድኑ ከሠለጠነች በኋላ በተለያዩ መድረኮች ለመወዛወዝ ዕድል ማግኘቷ እንደሚያስደስታት ትናገራለች፡፡ በአኬሻ ፌስቲቫል እንዲሁም በተለያዩ በዓላት ላይ ያቀረቡትን ትዕይንቶች ትጠቅሳለች፡፡ በቡድኑ ውስጥ ሙያቸውን ከማሳደግ በላይ እርስ በርስ መደጋገፋቸውን የምትናገረው ኤደን፣ ለወደፊት ቋሚ የሥልጠና ቦታ ቢኖራቸው ትመኛለች፡፡ 
ሁለቱም ታዳጊዎች ትዕይንት ሲኖቸው ቤተሰቦቻቸውን ይጋብዛሉ፡፡ ከቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ የሌሎች ታዳሚዎችን ድጋፍ ማግኘታቸው ሙያውን የበለጠ እንዲወዱት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ ሀብታሙና ኤደን እንደ አሠልጣኛቸውና የተቀሩት የተመስገን ልጆች አባላት በዓለም አቀፍ መድረኮች ባህላቸውን የበለጠ የማስተዋወቅ ሕልም እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
 
፡- ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
 
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ