****
በረሃውን ገነት የሚያደርገው ‹‹የነፍስ ምግብ››
አንድ ሊቅ ሰው ‹‹እኔ ጠንካራ ሠራተኛ ነው አእምሮዬ ሲደነዝዝ ቴኒስ በመጫወት እደሰታለሁ ኀዘኔን ልረሳው እንድችል ያደረገኝ ግን የተዋቡ ሙዚቆችን መስማት ነው፡፡›› አለ በእርግጥም በሰውና በዓለሙ መሃከል ፍጹም ሰላም ሰጭ ሁኖ የሚያስታርቀው የዕርቅ መሥዋዕት ጣዕም ያለው ዘፈንና ሙዚቃ ቃና ነው፡፡
ውብ ድምጽ ያላቸው ወፎች በረሃ ሃገራቸው ነው፡፡ ቃና ባለው ዜማ ከተዋበ ድምፃቸው ጋራ ሲዘምሩ ግን በረሃውን ገነት ያደርጉታል፡፡ እንዳዘነም ልብ የነበረውን ምድረ በዳ የገነት ያህል ሊለውጡት ችሎታ ሲኖራቸው አዳኞች አይተዋል፡፡ እንዲሁም የላባው ውበት ሊያኮራው የሚችል የቁራ አሞራ ደግሞ በዜማውና በድምጹ ክፋት እንደገነት ያማረችውን አገር በረሃ ያደርጋታል፡፡
ሰውም በሚኖርበት ርስቱ ላይ እንዲሁ ነው፡፡ የተዋጣ ቅያስ ባላቸው መንገዶች መጓዝ አይታው ሁሉ ደስ ያሰኘዋል፡፡
አበበቦችም በተተከሉበት ቦታ መጠለል አዲስ ስሜትና ዕረፍት ይሰጠዋል፡፡ ቅርፁ እጅግ አምሮ በታነፀ ቤት መኖርም ይመቸዋል፡፡ በሰገነት መቀመጥም እጅግ ክብር ያለው ሆኖ ያገኘዋል፡፡ ነገር ግን የነፍሰን አሥራው በማንቀሳቀስ ሰውን ደስ ሊያሰኘው የሚችል ጣዕም ያለው ሙዚቃና ባህል ያለው ዘፈን ባይኖር የማንኛውም የሚታይ ውበት ሁሉ ግምቱ አባይ ይሆናል፡፡
ተመስገን ገብሬ ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› (ኀዳር 1935)
**********
በቆልትን በወተት
ጥራጥሬን በቆልት አድርጎ መመገቡ ጤናን ለመጠበቅ ዓይነተኛ ዘዴ ነው፡፡ በተለይም የጥቁር ሽምብራ በቆልት ለሰውነት ኃይልን ከመለገስ ባሻገር በውስጡ የሚያካብታቸው፤ አያል ቫይታሚኖች የተስተካከለ ጤናን ያጎናጽፋሉ፡፡ ገብስ ባቄላና አተርን የመሳሰሉት ጥራጥሬዎች በበቆልት መልክ ተዘጋጀተው ለምግብነት ሲውሉ ጤናን ለመጠበቅ ይረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል እሸት ስንዴን ወቅጦና በውኃ በጥብጦ መጠጣቱም ጤናን ያደረጃል፡፡ ለጋው የስንዴ ጭማቂ አያሌ ሻይታሚኖች አሉት፡፡ በተለይም እርጉዘ ሴት ይህን ጨማቂ አዘውትራ ከተመገበች ጤናማ ቆንጆና ብልህ ልጅ ለመውለድ እንደሚያስችላት ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡ በሌላ በኩል ስንዴን በቆልት አድርጎ በእርጎ ወይም ከወተት ጋር ደባልቆ መጠጣቱም ሰውነትን እንደሚያጠናክር ጠበብቱ ያስረዳሉ፡፡ ከሌሎች በቆልት ጥራጥሬዎች የስንዴው ብቅል ወደር የለሽ ጠቀሜታ አለው፡፡ እርጅናን የሚከላከለው ቫየታሚን ‹‹ኤ›› በስንዴ ውስጥ በብዛት ይገኛል፡፡
*****
‹‹ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል››
‘ደብርዬ’ ደብሪቱ (ታላቅ እህታቸው እንደሚጠሩአቸው) ‘ረቂቅ’ ሴት ናቸው (ዘንድሮ ሰው ‘ክፉ’ አይባልም)፡፡
አበበች የሥልጣን፣ የጉልበት ችሎታ መጠኑ ገደቡ የት እንደሚደርስ መገመት ይከብዳታል፡፡ በቀጣፊነቱ የሚኮራ ጉልበታም ብቻ እንደሆነ በወ/ሮ ደብሪቱ ይገባታል፡፡
‹‹በይ እረዳሻለሁ›› አሏት፡፡
ነገሩም ሕመሙም አበሳጭቷት ተነጫነጨች፡፡
‹‹እንዴ? ምን ልሁን ነው … ጥጋብ እኮ ነው እናንተዬ›› አሉ፡፡
ወደ ሐያ የሚሆኑ የሽንኩርት እራሶች መክተፍ ነበረባት፡፡ ከማቀዝቀዣ የወጣ የበሬ ሽንጥ ሥጋ መክተፊያው እንጨት ላይ ቀይ የሕፃን ልጅ ሹራብ መስሎ ወድቆአል፡፡ የተባ ቢላ መሐሉ ላይ ተጋድሞ፡፡ ቢላውና ሹራቡ ሽርክ ይመስላሉ፡፡ ፍቅርኛ ነገሮች ምናምን …
‹‹ስልክ ላድርግ መጣሁ›› ብለው ወጡ ደብሪቱ፡፡
ሥራ የሚያመልጡበት ጥበባቸው ረቂቅ ነው፡፡ እንደ ባህላችንም ነው፡፡ ዛሬ የመሥራት አቅም ሲጠፋ፣ ሐሞት ሲሞት ፖለቲከኛ ይኮናል፡፡ ይቀላል፡፡ ማላገጥ ሕግና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡ ዓላማ ሳይደርስ ተመሃል ጎዳና እያቦኩ ቢቀርም … በሌላ እያሳበቡ መውደቅ ነው፡፡
‘ስልክ ልደውል’ ይሉና እንግዲህ ለሁለት ሰዓት ያህል ይጠፋሉ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ፈሳቸውን እየጠጣ ያ አልጋ አለማነጠሱ ደብሪቱ እራሳቸውንም ይገርማቸዋል፡፡ ጌትነትን ካልተኙበት ምኑ ጌትነት ሆነ፡፡ እመቤትነትም፡፡
ልጃቸው እንኳን አንድ ቀን አፏ ተስቶት ብትተቻቸው ‘አንቺም አልጋሽ የቢሮ ወንበር ነው’ ብለው ጆሮዋን ሲገርፏት እንደ ቀንድ አውጣ ተሰብስባ የሽሙጥና የኩርፊያ ልጋጓን ከመጐተት በስተቀር ቆማ አልመለሰችላቸውም፡፡ ማንንም ሰው ዝም የማሰኘት ችሎታ አላቸው፡፡
‹‹በል አንተ›› ብለው ሳይጠቁሙት ወሬ የሚጀምረውን ምሳሌ ጠቅሰው ‘መናገርን’ እስኪረግም ይወቁታል፡፡ መልካም ለመሆን ከፈለጉ ደግሞ የወደቀ ምራቅ ይመልሳሉ፣ ግመል ያሰክራሉ የአንድን የሰው ፀባይ የማያልቅ የሚቃረን የሚፋቀር ጐን ይሰጡታል፡፡ ‘ድንቅነት’ በእሳቸው ምላስ ሺሕ ፊት አላት … ‘ርግማን’ እልፍ ፊት አላት፡፡
እና ስልክ ለመደወል ቢጠፉ ለአካባቢው ሆነ ለማንም አይገርምም፡፡ የሚበቃ ምክንያት አላቸው፡፡ ባይኖርም ይሰጣሉ፡፡ ከሰጡ ደግሞ መቀበል ድንቅ ነው፡፡
አበባ ሥጋውን አመቻችታ ለመቁረጥ መስመር ስትፈልግ ልስላሴውና ቅዝቃዜው ማረካት፡፡ ቁርስዋንም ስላልበላች ቁርጥ ለመሞከር የድልህ ዕቃ አውጥታ ትንሽ ድልህ መክተፊያው ጣውላ ላይ ጠብ አድርጋ እየከተፈች አልፎ አልፎ ጥሬ ሥጋ እየዋጠች ሥራዋን ቀጠለች፡፡ ራስ ምታቱ ግን ኦ! ኦ! ያው ነው፡፡ ሻሽዋን አጠንክራ አናቷ ዙሪያ መጠምጠሙ ነው በትንሹም ቢሆን ያዋጣት፡፡
ስልክ መደወያ ቦታው በደብሪቱ የፈጠራ ችሎታ የሚወሰን ስለሆነ፣ ጭን የመሰለ ሰውነታቸውን ተሸክመው ማድ ቤት ሲገቡ መጀመሪያ ያዩት ግራ ጐኑ ላይ ቡግንጅ ያበቀለ የመሰለውን የአበባን ፊት ነው፡፡ ይሔ ቡግንጅ ደግሞ እንደ አናሳ ፍጡር ይነቃነቃል፡፡ ደማቸው ፈላ፡፡
‹‹ለራስሽ ደገስሽው?››
ቢላውን ቀምተው ቃጡባት ‹‹አንገቷን ማለት ነው›› አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ተደራሲያቸው ባይታይም፡፡ በነጠላ አይናገሩም ሲበሽቁ … የጐዳቸው አንድ ሰው ተከታይ አለው፤ እና ‹‹እናንተን ምን ማድረግ ይሻላል?›› ይላሉ … እሳቸውም ተከታይ አላቸው ግን አማራጭ ብዜቱን ገለልተኛ በግምት የሚመጠን ያደርጉታል፡፡
‹‹ምን ቢያደርጓቸው ይሻላል … ሴት ደረቅ እንጀራ አነሳት? … ቢበሉት ከቂጥ በላይ አይሆን … ‘ቂጣም ያሰኛል’›› አሉ፡፡
-አዳም ረታ ‹‹ሕማማትና በገና›› (2004)
*******
ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን
ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡
በአርእስቱ እንደተነገረው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋተ ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡
አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.
********
ኦሞትና ጉዑር ሁለቱ ወንድማማቾች
በኦፒው አምዎንግ የተተረከ የአኙዋ ተረት
በአንድ ወቅት ኦሞትና ጉዑር የተባሉ ወንድማማቾች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ኦሞት ሚስት ሲኖረው ጉዑር ግን የለውም ነበር፡፡ ወቅቱም የአዝመራ ወቅት ስለነበረ ኦሞት ሰብሉን ከወፎች የሚጠብቅበት ማማ ላይ ሆኖ ገብሱን እየጠበቀ ሳለ ጉዑር ደግሞ ባካባቢው ሆኖ ማሳውን ይመለከት ነበር፡፡ የኦሞትም ሚስት ለሁለቱም የሚሆን ምግብ ይዛ በመምጣት ከማማው ስር አስቀመጠችላቸው፡፡
ኦሞት ቁልቁል ሲመለከት ምግቡ ከእርሱ የሚተርፍ ባይመስለውም ከማማው ላይ ወርዶ በተመለከተ ጊዜ ምግቡ ለሁለቱም እንደሚበቃ አየ፡፡ ከማማው ላይ መውጣትና መውረድ ስለሰለቸውም እዚያው እማማው ስር ቁጭ ብሎ ለወንድሙ ሳይነግረው መብላት ጀመረ፡፡
እንዲህ ብሎም አሰበ “ምግቡን ሁሉ በልቼ ስለምጨርሰው ወንድሜም ሚስቴ ምግብ እንዳመጣችልን አያውቅም፡፡”
ነገር ግን ገንፎው በጣም ብዙ ስለነበር በልቶ መጨረስ አቃተው፡፡
ስለዚህ ወንድሙን ጠርቶ “ሳልጠራህ በላሁ፡፡ አሁን ፋንታህን ብላ፡፡” አለው፡፡
ሆኖም በሁኔታው በጣም አፈረ፡፡
የዚያን እለት ምሽት ከጨለመ በኋላ አብረው ወደቤት ሲመለሱ ኦሞት ጉዑርን እንዲህ አለው “ሚስት ታገባ ዘንድ ገንዘብ እሰጥሃለሁ፡፡”
እቤትም እንደደረሱ ለወንድሙ ሚስት ያገባ ዘንድ ገንዘብ ሰጠው፡፡ አዲሲቱም ሚስት ምግብ እያመጣችላቸው ሁልጊዜ አብረው ይመገቡ ጀመር፡፡
እሱም “ምንም ነገር ብትጠይቀኝ እሰጥሃለሁ፡፡” አለው፡፡
የዚህ ተረት መልዕክትም ሁለት ሰዎች አብረው ከኖሩ የየራሳቸው ንብረት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን አንደኛቸው ምንም ከሌለው እርስ በእርስ መተጋገዝና መረዳዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ያለው ለሌለው በመስጠት ሊረዳው ይገባል የሚል ነው፡፡
-ከኢትዮጵያ ተረቶች
No comments:
Post a Comment