Monday, October 27, 2014

ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለመጨመር ፈቃድ ጠየቀ

ግዙፉ የመካከለኛው ምሥራቅ አየር መንገድ ኳታር ኤርዌይስ፣ በሳምንት ሦስት ቀናት ከኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን የበረራ ቁጥር ለማሳደግ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ፈቃድ ጠየቀ፡፡
በኳታር ኤርዌይስ የኢትዮጵያ ቀጣና ኮሜርሺያል ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አንጁም ዓሊ ሚያን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገውን በረራ ቢቻል በቀን ሁለት ጊዜ ማድረግ ይፈልጋል፡፡ ሚስተር ሚያን አየር መንገዳቸው የበረራ ቁጥር የመጨመር ፍላጐት እንዳለው ገልጸው፣ ፈቃድ እንዲሰጠው ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን በቅርቡ ጥያቄውን አቅርቦ በመደራደር ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ በረራ የጀመረው በመስከረም 2005 ዓ.ም. ሲሆን፣ በሳምንት ሦስት ቀናት 144 መቀመጫዎች ባሉት ኤርባስ ኤ320 አውሮፕላን ከዶሃ አዲስ አበባ ይበራል፡፡ አየር መንገዱ በረራውን የጀመረው በኢትዮጵያና በኳታር መንግሥታት በተፈረመ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት የመግባቢያ ሰነድ አማካይነት ነው፡፡ ኳታር ኤርዌይስ 144 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ያሉት በመሆኑ፣ መንገደኞችን ከአዲስ አበባ ዶሃ ከወሰደ በኋላ ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት ያጓጉዛል፡፡
አየር መንገዱ ከአዲስ አበባ በርካታ መንገደኞች በማግኘት ላይ መሆኑን የገለጹት ሚስተር ሚያን፣ ለሁሉም አየር መንገዶች የሚበቃ ገበያ እንዳለ ጠቅሰው ከተፈቀደላቸው በቀን ሁለት ጊዜ ከዶሃ አዲስ አበባ ደርሶ መልስ በረራ ማድረግ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፍላጐታችን በቀን ሁለት ጊዜ መብረር ነው፡፡ የተቻለውን ያህል እንዲፈቀድልን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጋር እየተደራደርን ነው፤›› ብለዋል፡፡ 
ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የአቪዬሽን ባለሙያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዶሃ በረራ ባይኖረውም፣ የኳታር ኤርዌይስ ወደተለያዩ ክፍለ ዓለማት የሚበር በመሆኑ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ገበያ መሻማቱ አይቀርም ይላሉ፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ለኳታር ኤርዌይስ የሚፈቅደው ተጨማሪ የበረራ ቁጥር ውስን ይሆናል ያሉት ባለሙያው፣ ‹‹ባለሥልጣኑ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኃላፊዎች ጋር ይመክራል፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 13 ያህል የውጭ አየር መንገዶች ወደ አዲስ አበባ ይበራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ሉፍታንዛ፣ ኤሚሬትስ፣ ገልፍ ኤር፣ ፍላይ ዱባይ፣ ኬንያ ኤርዌይስ፣ ኢጅፕት ኤርና ተርኪሽ ኤርላይንስ ይገኙበታል፡፡
ኳታር ኤርዌይስ እ.ኤ.አ. በ1997 በአራት አውሮፕላኖች ሥራውን የጀመረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የ136 አውሮፕላኖች ባለቤት ሆኗል፡፡ ባለአምስት ኮከቡ አየር መንገድ በቅርቡ ግዙፍ የሆነውን ኤርባስ ኤ380 አውሮፕላን ተረክቧል፡፡ በተጨማሪም የቦይንግ ቢ 787 ድሪምላይነርና ቢ 777 አውሮፕላኖች ባለቤት ነው፡፡ አየር መንገዱ 70 ቢሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው 340 አዳዲስ አውሮፕላኖች አዟል፡፡
በአፍሪካ የገበያ አድማሱን እያሰፋ በመሆኑ በቅርቡ ከዶሃ ጂቡቲ አዲስ የበረራ መስመር እንደሚከፍት አስታውቋል፡፡ 
ኳታር ኤርዌይስ ወደ አዲስ አበባ በረራ የጀመረበትን አንደኛ ዓመት መስከረም 20 ቀን 2007 ዓ.ም. በቦራ የሕፃናት መዝናኛ ችግረኛ ሕፃናት ተማሪዎችን በማዝናናትና በመመገብ አክብሯል፡፡ ለተማሪዎቹ የመማሪያ ቁሳቁሶችንም አበርክቷል፡፡ 


No comments:

Post a Comment