Monday, September 21, 2015

እኛና ስልካችን


ሰሚት አካባቢ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ጊዜው ሕፃን አዋቂ ሳይባል በርካታ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በሚጾሙት ፍልሰታ ጾም ወቅት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ የተገኙት ምእመናን የቅዳሴ መጀመርን ይጠባበቃሉ፡፡
አንዳንዶቹ በፀጥታና በዝምታ ተቀምጠዋል፡፡ ፀሎት የሚያደርጉም አሉ፡፡ በሠላሳዎቹ መጨረሻ እንደምትሆን የገመቷት ወጣት ሁኔታ እንዳስገረማቸው አጠገቧ የነበሩት እናት ይናገራሉ፡፡ ወጣቷ ቤተ መቅደስ ገብታ ከተቀመጠች ጀምሮ እጇና ዓይኗ ከስልኳ አልተለዩም፡፡ አንዴም ቀና ሳትል በዚህ ሁኔታ ረዥም ደቂቃዎችን አሳለፈች፡፡ ቅዳሴ ተጀመረ ተጋመሰም፡፡ ወጣቷ ቅዳሴ ሲጀመር ያስቀመጠችውን ሞባይል ስልኳን አንስታ ከፍ አድርጋ በመያዝ ፀሎት እንደሚያደርግ ሰው ሁሉ አሁንም አሁንም ትሰግዳለች፡፡ ልጅቷን በመገረም ሲከታተሉ የነበሩት እናት ወዲያው በስልኳ የፀሎት መጽሐፍ እያነበበች እንደሆነ ተረዱ፡፡
ታክሲ ላይ፣ ካፍቴሪያ፣ በስበሰባ አዳራሽ ሌላም ሌላም ቦታ ላይ አንድ ጠረጴዛ ተጋርተው ተጠጋግተው የተቀመጡ ጓደኛሞች እንኳ እርስ በርስ ከመጫወት ይልቅ ስልካቸውን መርጠው በስልክ ሲጠመዱ መመልከት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ሁኔታው ሰዎች ከመቼውም በላይ ስልካቸውን የመረጡበት ጊዜ ነው ለማለት የሚያስደፍር ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ፣ ለማስተዛዘን ከለቅሶ ቤት ተገኝተው፣ የቤተሰብ እራት ላይ፣ ስብሰባ ላይ ወይም ክፍል ውስጥ ሰዎች መልዕክት በመላክ ወይም በመመለስ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመመልከት፣ ፎቶ በማንሳት አልያም በመነሳት መጠመድ በብዛት እየተስተዋለ ያለ ትዕይንት ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ስልካቸው ድምፅ አሰማም አላሰማም የትም ይሁኑ የት አሁንም አሁንም ስልካቸውን እያወጡ መመልከት ልምድ የሆነባቸው ይመስላል፡፡ ምንም ነገር እንዳያመልጠኝ በሚል ጥንቃቄ ወይም አንዳንድ ነገሮች፣ ኦን ላይን ያሉ ወዳጆች ቢያመልጡኝስ በሚል ሥጋት በማንኛውም ሰዓት የስልካቸውን ኢንተርኔት ኦን አድርገው የሚንቀሳቀሱም አጋጥመውናል፡፡
በሠላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ በአንድ የግል ተቋም ውስጥ ኤክስፐርት ነው፡፡ ሁልጊዜም ስልኩ ኦን መሆኑን በተደጋጋሚም ስልኩን እንደሚመለከት ይናገራል፡፡ በተለይም ኢንተርኔቱን ክፍት የሚያደርገው ማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ የሚወጡ ነገሮች እንዲያመልጡት ስለማይፈልግ፤ ኦንላየን ከሚያገኛቸው ጓደኞቹ ጋርም ማውራት (ቻት ማድረግ) ስለሚፈልግ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
‹‹ከጓደኞቼ ጋር ምሳ ልበላ ቁጭ ብዬ ስልኬን ዓየት ላደርግ እችላለሁ ግን ሳልቆይ ቶሎ አስቀምጣለሁኝ፡፡ ቤትም ሌላ ቦታም ስልኬን አየት አደርጋለሁኝ ግን ብዙ አልቆይም›› ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው በቀን የሀምሳ ወይም የመቶ ብር ካርድ የሚጨርስ ቢሆንም ይህን እንደ ችግር አይቆጥረውም፡፡ ምክንያቱም ከጓደኞቹ ጋር ቻት ማድረጉንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚወጡ ነገሮችን መከታተሉን እንደ ትልቅ ነገር ይመለከተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የብዙዎችን ስማርት ፎን መያዝ ተከትሎ ሰዎች ሁሉ ነገራቸው ከስልካቸው ጋር እየሆነ መሆኑን መታዘባቸውን ይናገራሉ አቶ ጌትነት አማረ፡፡ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የትምህር ጥናትና ምርምር ኤክስፐርት ናቸው፡፡ ‹‹ሻይ ቡና ለማለት ከጓደኛው ጋር ቁጭ ብሎ አጠገቡ ያለውን ጓደኛውን ትቶ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ካለ ጓደኛው ጋር ቻት የሚያደርግ ብዙ ሰው አለ፡፡›› የሚሉት አቶ ጌትነት፣ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ አብሮ ያለው ሰው እንዴት ስልኩ ላይ ከተጠመደው ሰው ጋር ሊያወራ ሊጫወትስ ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የራሳቸውን ቤተሰብ ጨምሮ በቤት ውስጥ፣ ቢሮና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ዕለት በዕለት እየታየ እንዳለ በመግለጽ የባሰ ያሉትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡
ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ጥናቷን በፕሮጀክተር በማቅረብ ላይ ያለችው ባለሙያ ጥያቄ ወይም አስተያየት ካለ ጠይቃ አሁንም አሁንም ስልኳ ወዳለበት ጥግ ሔደት እያለች ስልኳን ትመለከታለች፡፡ አንዴ ሁለቴ እንጂ አትደጋግመውም ብለው አሰቡ ታዳሚዎቹ፡፡ አቅራቢዋ ግን መለስ መለስ እያለች ስልኳን መነካካቷን ቀጠለች፡፡ ነገሩ የገረማቸው የሻይ ዕረፍት ላይ ለምን እንደዚያ እንደምታደርግ ጠየቋት፡፡ ከጠየቋት መካከል እሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡
የአቅራቢዋ መልስ ‹‹ስልኬን በተደጋጋሚ መመልከቴ እኔን ምንም አይረብሸኝም እናንተም የምትሰጡትን አስተያየት በደንብ ነው የምከታተለው›› የሚል ነበር፡፡ እሷ ብቻ ሳትሆን ከሰው መካከል ሆነው በስልካቸው የሚጠመዱ በአካል በተገኙበት ቦታ የሚካሔደውን ነገር ከልብ አትከታተሉም ሲባሉ እንከታተላለን መሳተፍም እንችላለን ብለው እንደሚከራከሩ ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁለትና ከዚያ በላይ ነገሮችን ለማድረግ መሞከር አስቸጋሪ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡
‹‹ሰው ትልቅ ጉዳይ ለማዋየት ቀጥራቸው እንኳ አሁንም አሁንም ስልካቸውን ከመመልከት የማይቦዝኑ አሉ፡፡ መነጋገር የሚያምረው ዓይን ዓይን እየተያዩ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሰው እንዴት ማውራቱን ሊቀጥል ይችላል? እኔ ከእንደዚህ ዓይነት ሰው ጋር ለመቀጣጠርም ፍላጐት የለኝም›› ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው እምነት የዚህ ዓይነቱ የሰዎች በሞባይል ስልክ መጠመድ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲሁም ጓደኝነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ትኩረት ሰጥተው ሊከውኑት የሚገባውን ነገር በአግባቡ እንዳይከውኑ ስለሚያደርግ ውጤታማነትን በጣም ይቀንሳል፡፡
ምንም እንኳ ዘወትር ሞባይል ስልክ ላይ የመጠመድ ነገር በታዳጊዎች ላይ የሚያይል ቢሆንም የተማሩና የተረጋጉ በሚሏቸው ጐልማሶች ላይ መታዘባቸውን በመጥቀስ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከብዙ ነገሮች አንፃር ስልክ በስልክ አይጠመዱም የሚባሉ ሰዎች እንኳ ከስልካችን አንለይ ያሉበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ሁሌም ስልክ ላይ መሆን ዘመን የተሻገሩ የማኅበራዊ እሴቶችን ይሸረሽራል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ሰዎች መቼ ነው ከስልክ ከኢንተርኔት ዓለም ውይይታቸው ራሳቸውን ገትተው በአካል በተገኙበት ቦታ ወዳሉ ሰዎች ትኩረታቸውን የሚመልሱት?›› ሲሉ በመጨረሻ ጥያቄአቸውን ይሠነዝራሉ፡፡
ትራፊክ ፖሊስ በማይኖርባቸው ቦታዎች ላይ ስልካቸውን እያዩ፣ መልዕክት እየመለሱና ስልክ እያነጋገሩ የሚያሽከረክሩ ጥቂት እንዳልሆኑ በአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ሕዝ ግንኙነት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ይገልጻሉ፡፡ አስረግጦ ለመናገር ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም በተደጋጋሚ ከሚታዩ አጋጣሚዎች በመነሳት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በስልክ ምክንያት የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ጥቂት እንደማይሆኑም ይገምታሉ፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ከተካተቱ 77 በመቶ የሚሆኑት መንገድ ላይ እየሔዱ በማንኛውም መንገድ ስልካቸውን መጠቀም ችግር የለውም ብለው የሚያስቡ ሲሆን፣ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት መደብር ውስጥ ተሰልፈው ወይም በሕዝብ መተላለፊያዎች ስልካቸውን መጠቀማቸው ችግር እንደሌለው ያምናሉ፡፡ ከ88 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቤተሰብ ተሰብስቦ እራት እየበላ፣ ስብሰባ ላይ፣ በፊልም ወይም በቴአትር አዳራሽ እንዲሁም በአምልኮ ቦታ ስልክ መጠቀም ተገቢ አይደለም ብለው የሚያምኑ ቢሆንም ተግባራቸው ግን በተቃራኒው መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡
የሰዎች ሁልጊዜም ስማርት ፎናቸውን ኦን ማድረግና ስልካቸውን ሳይመለከቱ ደቂቃዎች እንዲያልፉ አለመፈለግ ከፍተኛ ችግር እየሆነ መሆኑን ጥናቱ ይደመድማል፡፡ የመደምደሚያው መሠረት የሰዎች በእውነተኛው ዓለም ከጐናቸው ከተቀመጠ ሰው ይልቅ ትኩረታቸው በስልክ ሲያዝና ፍላጐታቸው በአካል አብሯቸው ካልሆነ ሰው ጋር መነጋገር መሆን መሠረታዊ የሰው ልጆችን የግንኙነት ዘዬ ይረብሻል የሚል ነው፡፡ በጥናቱ የተጠቀሰው ሌላው ችግር ደግሞ አጠገብ ካለ ሰው ይልቅ በስልክ የመጠመድ ነገር በፊት በፊት ይተች የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተቀባይነት እያገኘና እንደ መደበኛ ነገር እየተቆጠረ ብዙዎችም እዚህ መስመር ውስጥ እየገቡ መሆኑ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ኢዛና ዐምደወርቅ በሞባይል ስልክ የመጠመድ ነገር በስፋት እየታየ መሆኑን ይህም በራሳቸው ዋጋ ያላቸውን ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እየረበሸ ሰዎችን ወደ አርቴፊሻል ግንኙነቶች እያሻገረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ቀን በትምህርትና በሥራ ተወጥረው የማይገናኙና የማይተያዩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ምሽት ላይ ለግማሽ ወይም ለአንድ ሰዓት ራት ላይ ሲገናኙ እንኳ ስልካቸውን ለመተው አለመፈለግ የችግሩን ስፋት እንደሚያሳይ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ተለምነው እራት የሚበሉም አሉ፡፡ በሕይወታቸው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ካላቸው ቤተሰቦቻቸው ይልቅ ከማያይዋቸው ሩቅ ካሉ ምናልባትም እየቆዩና በመሀል እየጠፉም ከሚመልሱላቸው ጓደኞቻቸው ጋር ቻት ማድረግን የሚመርጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ የኢንተርኔት ግንኙነት በብዙ መልኩ እውነተኛውን ግንኙነት አይስተካከለውም አርቴፊሻል ነው፡፡›› ይላሉ፡፡
በስልክ መጠመድ እንደ አዲስ አበባ ባሉና በሌሎች ትልልቅ ከተማዎች ብቻም ሳይሆን በትንንሽ ከተሞችም ቦታ ሳይመረጥ መማሪያ ክፍል፣ ለቅሶ ቤት፣ ሠርግ ላይ እንዲሁም ትልልቅ አገራዊ ስብሰባዎች ላይም እየተስተዋለ መሆኑን መታዘባቸውን ይናገራሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ስብሰባዎች ላይ ወይም ክፍል ውስጥ ሆኖ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ማየት ወይም የስልክ መልዕክት ማንበብም ሆነ መመለስ እንደተለመደ ነገር እየታየ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ስማርት ፎን ይዞ መታየት የሚያኮራ ነገር ሆኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በተለይም ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ፎኖች ገበያውን በማጥለቅለቃቸው ሊቀየር ችሏል፡፡ እንደ ህዋዌ፣ ቴክኖና ዜድቲኢ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች በዚህ ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተጠቃሚዎች የሚሆኑ ስልኮችን የሚያቀርበው ሳምሰንግም በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው፡፡
እየጨመረ ያለውን የሰዎችን በስማርት ፎን መጠመድ በመመልከት የተለያዩ አገሮች ለችግሩ ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ በኢንተርኔትና እንደ ሞባይል ባሉ ዲጂታል ቁሶች መጠመድ እንደማንኛውም ሌላ ሱስ እንዲታይ ማድረግ የመጀመሪያው ዕርምጃ ሲሆን፣ ከዚህ ሱስ ማገገቢያ ማዕከል እስከማዘጋጀት የገፉም አሉ፡፡ ለምሳሌ በሴንጋፖር በስልክ ሱስ ለተያዙ የምክር አገልግሎት ማዕከሎች አሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ ሱስ እንደ አእምሯዊ ጤና መዛባት መታየት አለበት የሚል ክርክር የሚያነሱ የሥነ አእምሮ ሐኪሞችም አሉ፡፡
ቀደም ሲል ከስማርት ፎኖች ጋር በተያያዘ ጐልቶ ይታይ የነበረው ችግር በሞባይል ጌሞች መጠመድ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማኅበራዊ ድረ ገጾች ሱስ እያየለ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ::
ምንጭ:http://ethiopianreporter.com

‹‹የመንግሥት አመራር በሙሉ ሙስና ስለፈጸመ ስብስብ አድርጋችሁ የምታደርጉትን አድርጉ የሚል መልዕክት አልደረሰኝም››

ባለፈው ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣ ከጋዜጠኞች ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ መንግሥታዊው ሥርዓት በሙስና ውስጥ
መዘፈቁን በግልጽ እየተናገረ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ግን በመናኛ ጉዳዮች ላይ አተኩሯል የሚል ነው፡፡ የፖለቲካና የሕግ ቋንቋ የተለያዩ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ዓሊ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዕርምጃ የሚወስደው በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ጉባዔ ወቅት በሙስና ላይ ቁርጠኛ የሆነ አመራር አለመሰጠቱና ሙስናን መታገል አለመቻሉ ቢገለጽም፣ እከሌ ሙሰኛ ነው ተብሎ መረጃ ባለመቅረቡ ወደ ሕግ ለመሄድ አይቻልም ብለዋል፡፡ መንግሥት አሁንም ሙስናን ለመታገል ቁርጠኛ መሆኑንና እሳቸውም የተረዱት በዚህ መንገድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የመንግሥት አመራር በሙሉ ሙስና ስለፈጸመ ስብስብ አድርጋችሁ የምታደርጉትን አድርጉ የሚል መልዕክት አልደረሰኝም፤›› ያሉት አቶ ዓሊ፣ ከሙስና ጋር በተያያዘ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡዋቸው ምላሾች በ ቢዝነስና ኢኮኖሚ ገጽ ላይ ተስተናግደዋል፡፡

ምንጭ:http://www.ethiopianreporter.com

ታሪክን የኋሊት

መስከረም 06፣2008
የጀርመን ናዚዎች፣ ዓለምን የመቆጣጠር ክፉ ኃሳብ ባደረባቸው ጊዜ፣ ክፉ ኃሳባቸውን ፖላንድን በመውረር አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ አገሪቱን፣ በ20 ቀናት ሙሉ ለሙሉ፣ በመዳፋቸው አስገቧት፡፡ ፓላንዳውያን ፣አገራቸውን ከናዚዎች ወረራ ለመከላከል፣ የተቻላቸውን አደረጉ፡፡ የናዚዎች ዘመቻ፣ 16ኛ ቀኑን ባስቆጠረ ማግስት፣ ከምስራቅ አቅጣጫ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ቀይ ጦር ወረራ መክፈቱ፣ ለፖላንዳውያኑ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባቸው፡፡ ይህ ከሆነ፣ ዛሬ ልክ 76 ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡ ጀርመኖቹ ወረራ በጀመሩ በ20 ቀናቸው፤ ሶቪየቶቹ በ4 ቀናት ውጊያ ፖላንድን ተቃረጧት፡፡ ሶቪየት ህብረት፣ የፖላንድን ምስራቃዊ ግዛት የያዝኩት፣ የዩክሬንና የቤሎሩሲያን ግዛቶቼን ደህንነት ለማስጠበቅ ነው፣ የሚል ምክንያት አቀረበች፡፡
እውነታው ግን፣ ፖላንድ፣ በጀርመን ናዚዎች ልትወረር አንድ ሳምንት ሲቀራት፣ በጀርመንና በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ በተፈራረሙት፣ ሚስጥራዊ ስምምነት መነሻ ነበር፡፡ ሚስጥራዊው ስምምነት፣ የዚያን ጊዜዎቹን የሁለቱን አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስም በመያዝ፣ በታሪክ የሪቨንትሮፕ ሞሎቶቭ ስምምነት ተብሎ ይታወቃል፡፡ ስምምነቱ፣ ላይ ላዩን ያለመጠቃቃት ውለታ ቢመስልም፣ ሚስጥራዊ ክፍሉ የግዛት መሸንሰንና የተፅዕኖ ክልልን መፍጠርን የተመለከተ ነው፡፡ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት፣ የፖላንድን ምስራቃዊ ግዛት የያዘችውና ሦስቱን የባልቲክ አገሮች ኢስቶኒያ፣ላቲቪያና ሊትዌንያን ወደ ራሷ የቀላቀለችው፣ በዚሁ ሚስጥራዊ ስምምነት መነሻ ነው ይባላል፡፡ የሶቪየት ህብረትና የናዚዎቹ ያለ መጠቃቃት ውለታም ሆነ፣ ሚስጥራዊው ስምምነት፣ ብዙ ርቀት አልተጓዘም፡፡ የጀርመን ናዚዎች፣ ስምምነቱን ሶቪየት ህብረትን ለማዘናጋት ተጠቅመውበታል፡፡ ናዚዎቹ አቅማቸው መፈርጠሙ በተሰማቸው ጊዜ፣ ከሞስኮ ጋር የገቡትን ያለመጠቃቃት ውለታ አሸቀንጥረው ጣሉት፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ፣ ናዚ ጀርመን ሶቪየት ህብረትን ወረረች፡፡ ወረራው የቀድሞዋን ሶቪየት ህብረት በጦርነቱ ከተሳተፉ አገሮች ሁሉ፣ የላቀውን ዋጋ አስከፈላት፡፡ የ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ ዋነኛዋ ቀንበር ተሸካሚ ሆነች፡፡ ሌላ ሌላው፣ ጥፋትና ውድመት፣ ወደ ጐን ቢባል እንኳ ፣ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጐቿን ሕይወት አስገብሯታል፡፡

ምንጭ:shegerfm.com

ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ አለምን እየመራ ነው አዲስ አልበሙ፣ በሳምንት 412 ሺህ ኮፒ ተሽጦለታል

“ዘ ዊኪንድ” በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ፣ ባለፈው ሳምንት በአለም ደረጃ በቢልቦርድ ምርጥ አልበሞችሰንጠረዥ የ1ኛነትን ደረጃ በዚህ ሳምንትም አለምን እየመራ ይቀጥላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተዘገበ፡፡“ቢዩቲ ቢሃይንድ ዘ ማድነስ” የተሰኘው አዲሱ የአቤል አልበም፣ ለገበያ በቀረበበት የመጀመሪያው ሳምንት በሽያጭ ብዛት መሪነቱን እንደሚይዝ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም፣ ከተገመተው በላይ እንደተሳካለት ፎርብስ ዘግቧል፡፡ በ350 ሺህ የአልበም ሽያጭ አንደኛ እንደሚሆን የተገመተው የአቤል አልበም፣በ412 ሺህ ያህል ተቸብችቧል፡፡ በአዲሱ አልበሙ ውስጥ የተካተቱት 12 ሙዚቃዎችም በያዝነው ሳምንት የቢልቦርድ 50 ምርጥ ሙዚቃዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ካለፉት ሰባት አመታት ወዲህ፣ በቢልቦርድ የምርጥ ዘፈኖች ሰንጠረዥ፣ በአንድሳምንት ሁለት ዘፈኖቹ፣ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ባለው ደረጃ ውስጥየተካተቱለት የመጀመሪያው ወንድ ድምጻዊ አቤል ተስፋዬ ብቻ መሆኑን ቢል ቦርድ ገልጿል የሰሞኑን የአቤል ስኬት ሲዘግብም፤ በ57 አመታት የቢልቦርድ ሰንጠረዥ ታሪክ፣ አቤል በአንድ ሳምንት ውስጥ ብዙ ዘፈኖቹ፣ በምርጥ 100 ዘፈኖች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱለት ስድስተኛው ድምጻዊ ነው ብሏል፡፡ ዘንድሮ፣ በአንድ ሳምንት ውስጥ፣ ከአቤል የአልበም ሽያጭ የሚበልጥ ሪከርድ ያስመዘገበ ድምፃዊ የለም ከድሬክ በስተቀር፡፡ አመቱ የአቤል ተስፋዬ ነው ያለው ፎርብስ መጽሄት፤ የድምጻዊው የሙዚቃ ስራዎች የካናዳንና የአሜሪካን ሬዲዮ ጣቢዎች በስፋት መቆጣጠራቸውንና ከፍተኛ ተወዳጅነት ማትረፋቸውን ዘግቧል፡፡ የአቤል ዘፈን በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያዎች በብዛት በመሰራጨት አቻ አልተገኘላትም፡፡ “ስድ” ቃላትን በሙዚቃዎቹ ውስጥ ይደጋግማል በሚል ትችት የሚሰነዘርበት አቤል ተስፋዬ፤ በሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያዊኛ ቃና ይንፀባረቃል የሚለው አስተያየት ከሁሉም በላይ እንደሚያስደስተው ገልጿል፡፡ በዘፈን መሃልም አልፎ አልፎ አማርኛ ያስገባል፡፡