Sunday, October 26, 2014

የተመስገን ልጆች





የሸራተን አዲስ ቦልሩም አዳራሽ መድረክ ላይ በዘመነኛ ዘዬ የተሠሩ ባህላዊ አልባሳት የለበሱ ሞዴሎች ይታያሉ፡፡
የፋሽን ትዕይንት አሳይተው ከመድረኩ ከወረዱ በኋላ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ያሉ ታዳጊዎች በተርታ መድረኩ ላይ ወጡ፡፡ ታዳጊዎቹ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በጉራጊኛ፣ በትግርኛና በሌሎችም ቋንቋዎች በተዜሙ ሙዚቃዎች እየታጀቡ ይወዛወዛሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከሚያዋሰኑ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዜማዎችን እየተከተሉም ይደንሱ ነበር፡፡ ከአፍሪካና ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች የመጡና በአዳራሹ የነበሩት ታዳሚዎች በተመሳሳይ ስሜት የታዳጊዎቹን ትዕይንት እያጣጣሙ ነበር፡፡
ይህን ድባብ ያስተዋልነው ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ በአና ጌታነህ በተዘጋጀው ‹‹አፍሪካን ሞዛይክ›› ዓመታዊ የገቢ ማሰባሰቢያ የፋሽን ትዕይንት ላይ ነበር፡፡ በትዕይንቱ እኩሌታ ላይ ባህላዊ ውዝዋዜ ያቀረቡት ታዳጊዎች በ2007 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ከተካሄዱ ኮንሰርቶች አንዱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ አዲሱን ዓመት ለመቀበል በሚሌኒየም አዳራሽ የተሰባሰቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ቴዎድሮስ ታደሰን ተከትለው ወደ መድረክ የመጡትን ታዳጊዎች በድምቀት ነበር የተቀበሏቸው፡፡ 
በተለያዩ ብሔረሰቦች ሙዚቃዎች ያለማቋረጥ ያሳዩትን ውዝዋዜ ከቡድኑ አባላት ጥቂቱ የቆዳ ከበሮ በእጃቸው እየመቱ ያጅቡ ነበር፡፡ የተቀሩት ታዳጊዎች እጃቸውና እግራቸውን በሰንሰለት ታስረው ከሰንሰለቱ ለመውጣት እየተጣጣሩ ይደንሱ ነበር፡፡ ወደ 150 የሚጠጉት ታዳጊዎች ሰንሰለቱን ከበጠሱ በኋላም ውዝዋዜያቸውን ቀጥለዋል፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ከአንድ ብሔር ወደ ሌላው እየለወጡ ወደ አንድ ሰዓት ገደማ መድረኩን ተቆጣጠሩ፡፡
ታዳሚዎቹ በጭብጨባና በጩኸት ታዳጊዎቹን እያጀቡ ነበር፡፡ ከስምንት ዓመት ልጅ ጀምሮ በቡድናቸው የሚገኘው ታዳጊዎች ‹‹የተመስገን ልጆች›› ናቸው፡፡ የተመስገን ልጆች ወደ 300 የሚጠጉ አባላት ያሉት የባህል የውዝዋዜ ቡድን ሲሆን፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በትልልቅ መድረኮች ላይ ለረዥም ሰዓት በሚያሳዩት ትዕይንት ታዋቂ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት መድረኮች አባላቱን በቅርብ ካየንባቸው መካከል ናቸው፡፡ የተመስገን ልጆች በሚሳተፉባቸው ዝግጅት ታዳሚዎቻቸውን በኅብረት የሚያስደምም ትዕይንት ያቀርባሉ፡፡ መድረክ ላይ ሲወዛወዙ ከፊት ለፊት የሚታዩት ሕፃን የቡድኑ አባላት የብዙዎችን ቀልብ ይገዛሉ፡፡
የተመስገን ልጆች የተሰባሰቡትና የሚሠለጥኑበት በተወዛዋዥ ተመስገን መለሰ ነው፡፡ ቡድኑ ከስምንት ዓመት በፊት በ37 አባላት ነበር የተመሠረተው፡፡ ተመስገን ወደ ውዝዋዜ የገባው ልጅ ሳለ ነበር፡፡ የቤተሰቡ መኖሪያ ቤት ያለ አነስተኛ ሳጥን እንደ መድረክ ተጠቅሞ ቤተሰቦቹን በእስክስታ ያዝናና ነበር፡፡ ሸማኔ አባቱና ሠዓሊ ወንድሙ ለጥበባዊ ጉዞው እገዛ እንዳረጉለት የሚናገረው ተመስገን፣ ወደ ሙያው ዘልቆ እንዲገባ መንገድ የከፈተለትን ‹‹ትንሹ ሙዚቀኛ›› ድራማ ያስታውሳል፡፡ በተወለደበት አካባቢ የተቋቋመ የቀበሌ ኪነት ቡድን አባል ስለነበር በድራማው መሳተፍ ችሏል፡፡
‹‹ትንሹ ሙዚቀኛ›› በቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የልጆች ክፍለ ጊዜ የተላለፈ ድራማ ነበር፡፡ ድራማው ሙዚቃ በሚወድ የንጉሥ ልጅ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ተመስገን የንጉሡ ቧለሟል ሆኖ ይተውናል፡፡ ልዑሉ ከቤተ መንግሥት ተደብቆ ክራር ሲጫወት ቧለሟሉ እየሰለለ ለንጉሡ በመንገር ያደናቅፈዋል፡፡ ገጸ ባሕሪው በሠፈሩ ልጆች እንዲጠላ ቢያደርገውም በሥራው የተዋወቃቸው ሰዎች ወደ ለሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር መርተውታል፡፡
በወቅቱ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ስለመኖሩ እንኳን የማያውቀው ተመስገን መግቢያ ፈተና አልፎ ቴአትር ቤቱን ሲቀላቀል የ12 ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ዘወትር ከትምህርት መልስ በቴአተር ቤቱ ሥልጠና ይወስዳል፡፡ በየሳምንቱ መጨረሻ ከዕድሜ እኩዮቹ ጋር ውዝዋዜ ያቀርባሉ፡፡ በየወሩ 20 ብር እየተከፈው ለስድስት ዓመት ከሠራ በኋላ በ1995 ዓ.ም. ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ሲያቀና ዕድሜው ስላልደረሰ ከትልልቅ ተወዛዋዦች ጋር ተደርቦ እንዲሠራ ተደርገ፡፡ ከዓመታት በኋላ የቴአትር ቤቱ የውዝዋዜ ቡድን በሚያቀርባቸው ትዕይንቶች ላይ በዋነኛነት መሳተፍ ጀመረ፡፡
ተወዛዋዥ የመሆን ሕልሙ የሕፃናትና ወጣቶች ቴአትር ከዛም የሀገር ፍቅር ቡድን አባል በመሆኑ ቢሳካም ብዙ ታዳጊዎች ዕድሉን አለማግኘታቸው ያሳዝነው እንደነበረ ተመስገን ይናገራል፡፡ ሀገር ፍቅር እያለ 37 ታዳጊዎችን አሰባስቦ ማሠልጠን የጀመረውም ለታዳጊዎቹ ተስፋ ለመስጠት ነበር፡፡ የተመስገን ልጆች የመጀመሪያ ዙር ሠልጣኞች ሲመረቁ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ በአንድ መድረክ ማቅረባቸውና ትዕይንቱ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ይቀርብ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የተመስገን ልጆች ቀስበቀስ በቁጥር ከጨመሩ በኋላ ከሙዚቃ ክሊፕ አንስቶ በተለያዩ መድረኮች ታይተዋል፡፡ የነፃነት መለሰ ‹‹ባይ ባይ›› እና የመስፍን መለሰ የጉራግኛ ሙዚቃ ክሊፖች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በቅርቡም በተካሄዱት ዓለም አቀፍ የሆቴሎች ፎረም ላይና የአፍሪካ እግር ኳስ ኮን ፌዴሬሽን (ካፍ) ስብሰባ ላይ ትርዒት አቅርበዋል፡፡ ‹‹እብዶች ናችሁ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ተውኔት አዘጋጅተው ያቀረቡ ሲሆን፣ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ፣ ጎተ፣ በኢጣልያ ባህል ማዕከል፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና በሌሎችም መድረኮች ላይ ሥራቸውን አሳይተዋል፡፡
አባላቱ ተፈትነው ቡድኑን ከተቀላቀሉ በኋላ በነፃ ይሠለጥናሉ፤ በሚጋበዙበት መድረክ ሥራቸውን ያቀርባሉ፡፡ ተመስገን እንደሚለው ልጆች ቀላል ከሚባል ትዕይንት ውጪ ማሳየት አይችሉም የሚል የተሳሳተ ግምት አለ፡፡ ፍላጎትና ችሎታ ያላቸው ልጆች መድረክ አለማግኘታቸው በሙያው መዝለቅ እንደማይቻል ሆኖ እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ያለፈው የ29 ዓመት ወጣት ተመስገን ለታናናሾቹ የተሻለ መድረክ ለመስጠት ያቋቋመው ቡድን አያሌ ፈተናዎች ማለፉን ይናገራል፡፡
ልጆች ለማሠልጠን በመፈለጉ ከቤተሰቡ ጋር እስከመጋጨትና አጋዥ ማጣት ድረስ ቢያደርሰውም ቡድኑ አለመበተኑን በደስታ ተሞልቶ ይናገራል፡፡ ተመስገን እንደሚለው፣ ማንኛውም ሰው ስኬት ላይ ከመድረሱ በፊት የሚደግፈው ጥቂት ሰው ብቻ ነው፡፡ ‹‹ቤተሰብም ቢሆን አንድ ደረጃ ላይ ተደርሶ ካላየ አያበረታታም፤ አብዛኛው ወላጅ ትልቅ ደረጃ ደርሰው እስኪታይ ድረስ ልጁ ወደዚህ ጥበብ እንዲገባ አይፈልግም፤›› ይላል፡፡
የቡድኑ አባላት መድረክ ማግኘታቸው ተቀባይነት እንደሚያስገኝላቸው ያምናል፡፡ በእርግጥ ቋሚ መለማመጃ ቦታ የላቸውም፡፡ በተለይ በርካታ ተወዛዋዥ የሚያስፈልገው ትዕይነት ሲኖር ሰፊ ቦታ ተከራይተው ይለማመዳሉ፡፡ ለሙያው ያላቸው ፍቅር ጥንካሬ እንደሚሰጣቸው የሚያምነው ተመስገን፣ ተወዛዋዦች እንደ ዘፈን ማጀቢያ ብቻ ሳይሆን ለብቻቸውም መሥራት እንደሚችሉ ማሳየታቸው ሁነኛ ስኬታቸው እንደሆነ ይገልጻል፡፡ 
እንደ ተመስገን፣ ለውዝዋዜ ሙዚቃ ቢያስፈልግም ተወዛዋዦች ከሙዚቀኛ ተነጥለው ትዕይንት ማቅረብ አይችሉም ማለት አይደለም፡፡ ሙዚቃ እያጀባቸው ውዝዋዜ ጎልቶ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ያስረግጣል፡፡ ሌላው የተመስገን ስኬት ታዳጊዎች መሥራት የሚችሉትን ማሳየታቸው ነው፡፡ ትልልቅ መድረክ ላይ መካፈላቸው ትኩረት ያልተሰጣቸውን ታዳጊዎች የሚያበረታታ መሆኑን ይናገራል፡፡ ተመስገን ወሳኙ ዕድሜ ሳይሆን የውስጥ ፍላጎትና መሰጠት ነው ይላል፡፡
ተመስገን ከምንም በላይ በተመስገን ልጆች እንዲደሰት የሚያደርገው  ተቀባይነት ማግኘታቸው ነው፡፡ ‹‹ከተለያየ አገር ወይም ሙያ የመጡ ሰዎችን ቀልብ መግዛታችን ስኬታችን ነው፡፡ አንድ ትዕይንት ተጠናቆ ተመልካች ቆሞ ሲያጨበጭብ መመልከት በዋጋ አይተመንም፤›› ይላል፡፡
የተመስገን ልጆች ለሚጋበዙባቸው መድረኮች የተገባ የሚሉትን መልዕክት የሚያስተላልፍ ውዝዋዜ ያቀርባሉ፡፡ እንደ ምሳሌ በአፍሪካን ሞዛይክ ያሳዩት አልባሳት ላይ ያተኮረ ውዝዋዜና በካፍ ስብሰባ ወቅት ያቀረቡት እግር ኳስን የማካለ ትዕይንት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ተመስገን እንደሚለው፣ በየመድረኩ ገንቢ የሚሉትን መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ የ2007 ዓ.ም. የእንቁጣጣሽ ኮንሰርት ላይ እጅና እግራቸውን ታሰረው የተወዛወዙት ከድህነት፣ ከኋላቀርነት፣ ከማይምነትና ከመሳሰሉት ነፃ መውጣትን ለማሳየት ነው፡፡ እንደ ተወዛዋዦቹ ገለጻ፣ ተመልካች በየራሱ አየያይ ሊተረጉመው ቢችልም በውዝዋዜያቸው የነፃነትና ጥንካሬን ፅንሰ ሐሳብ ያስተላልፋሉ፡፡ 
በብዛት የኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ላይ ቢያተኩሩም አስፈላጊ ሲሆን የተለያዩ  አገሮች ዳንስ ያቀርባሉ፡፡ ለተጠሩበት ትዕይንት አስፈላጊ ከሆነ ከድረ ገጽ ወስደው ይለማመዳሉ፡፡ አምና ክሮሺያውያን በጋበዟቸው መድረክ ላይ የክሮሺያ ባህላዊ ዳንስ አጥንተው ማቅረባቸውን ተመስገን ጠቅሷል፡፡
እስካሁን ወደ 15 የሚደርሱ የውዝዋዜ ዘዬዎችን በአንድ ትዕይንት አካተው ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በየጊዜው አዳዲስ ዘዬ ለማጥናት የሚሞክሩ ሲሆን፣ ሙዚቃቸውን ማግኘት የቻሉትን ብሔረሰብ ባጠቃላይ ያካትታሉ፡፡ ከስምንት ዓመት አንስቶ ያሉ ልጆችን ለረዥም ሰዓት ያለማቋርጥ መድረክ ላይ እንዲጫወቱ ለማድረግ ተከታታይ ልምምድ ማድረጋቸው ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ተመስገን ያስረዳል፡፡ እሱ እንደሚለው ሥልጠናው ወደ ቡድኑ የሚመጡ ታዳጊዎች ማንኛውንም ነገር መሥራት እንደሚችሉ ከማሳመን ይጀምራል፡፡ ‹‹ሙያውን ወደውት ስለሚሠሩ የሚሳናቸው ነገር አይኖርም፤›› የሚለው ተወዛዋዡ፣ የታዳጊዎቹ ልዩ ጥምረት ተመልካችን እንደሚማርክ ይናገራል፡፡
የቡድኑ አባላት ሥልጠና እየወሰዱና ትዕይንት እያቀረቡ በተመስገን ልጆች ክበብ ውስጥ መቆየት እስከፈለጉበት ጊዜ ይቆያሉ፡፡ ተመስገን ከቡድኑ ጎን ለጎን በቶቶት የባህል ቡድን ውስጥ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም የሙዚቃ ክሊፖችን ያዘጋጃል፤ የውዝዋዜ ኬሮግራፈርም ነው፡፡ ከተለያዩ ከተማዎች ለሚመጡ የባህል ቡድኖች የውዝዋዜ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በቅርብ አንድ ተወዛዋዥ የሚያልፍበት ውጣ ውረድ ላይ ትኩረት ያደረገ ‹‹መቅረዝ›› የተሰኘ ፊልም ያወጣል፡፡
መስቀል አደባባይን የመሰሉ ሰፊ ቦታዎች ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተወዛዋዦችን አቀናጅቶ ትዕይንት ማቅረብ ለወደፊት ከሚመኛቸው ውስጥ ነው፡፡ የተመስገን ልጆች በዓለም አቀፍ መድረኮች ተገኝተው የኢትዮጵያን ባህላዊ ውዝዋዜ ማስተዋወቅ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ከቅርብ ጊዜ ዕቅዳቸው አንዱ ነው፡፡
ከተመስገን ልጆች አባላት አንዱ ሀብታሙ ደረጀ የ14 ዓመት ታዳጊ ነው፡፡ በውዝዋዜው የቀድሞውን ወወክማ የተቀላቀለው ልጅ እያለ ነበር፡፡ ወወክማ ውስጥ ሥልጠና ከመውሰዱ በተጨማሪ የድምፃዊ ወንድሙ ተወዛዋዥ ጓደኞች ውዝዋዜ ያስተምሩት ነበር፡፡ ወደ ተመስገን ልጆች ቡድን ከተቀላቀለ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ መድረክ ላይ የተወዛወዘበትን የአፍሪካን ሞዛይክ ዝግጅት ያስታውሳል፡፡
ቀጥሎ በሸራተን አዲስና በትዝታ ፌስቲቫል ላይ ያቀረባቸው ውዝዋዜዎችን በሐሴት ተሞልቶ ያወሳል፡፡ በተለይም የጎጃምና ጉራግኛ ውዝዋዜ የሚወደው ሀብታሙ፣ ትምህርት ጨርሶ የሙሉ ጊዜ ተወዛዋዥ የሚሆንበትን ቀን በጉጉት እንደሚጠባበቅ ይናገራል፡፡
ሌላዋ የቡድኑ አባል ኤደን ተኮላ ውዝዋዜ የጀመረችው አዲስ ቤዛ በተሰኘ ቡድን ውስጥ ነበር፡፡ የተመስገን ልጆችን ከተቀላቀለች አንድ ዓመት ሆኗታል፡፡ በቡድኑ ከሠለጠነች በኋላ በተለያዩ መድረኮች ለመወዛወዝ ዕድል ማግኘቷ እንደሚያስደስታት ትናገራለች፡፡ በአኬሻ ፌስቲቫል እንዲሁም በተለያዩ በዓላት ላይ ያቀረቡትን ትዕይንቶች ትጠቅሳለች፡፡ በቡድኑ ውስጥ ሙያቸውን ከማሳደግ በላይ እርስ በርስ መደጋገፋቸውን የምትናገረው ኤደን፣ ለወደፊት ቋሚ የሥልጠና ቦታ ቢኖራቸው ትመኛለች፡፡ 
ሁለቱም ታዳጊዎች ትዕይንት ሲኖቸው ቤተሰቦቻቸውን ይጋብዛሉ፡፡ ከቤተሰቦቻቸው በተጨማሪ የሌሎች ታዳሚዎችን ድጋፍ ማግኘታቸው ሙያውን የበለጠ እንዲወዱት እንዳደረጋቸው ይናገራሉ፡፡ ሀብታሙና ኤደን እንደ አሠልጣኛቸውና የተቀሩት የተመስገን ልጆች አባላት በዓለም አቀፍ መድረኮች ባህላቸውን የበለጠ የማስተዋወቅ ሕልም እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡
 
፡- ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
 
ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment