Tuesday, October 14, 2014

የኢራፓ ም/ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ፓርቲውን ለቀቁ

በፕሬዚዳንቱ አምባገነንነትና ኢሕአዴግ በሰጠው ገንዘብ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል
- ‹‹አመራሮቹ የተናገሩት ሁሉ ሐሰት ነው›› የፓርቲው ፕሬዚዳንት
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ፣ አምስት የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አመራሮች ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ተሾመ ወልደ ኃዋርያት፣ አቶ ደረጀ ግርማ፣ ወ/ሪት መስታወት ስመኝ፣ አቶ ማሙሸት መኮንንና አቶ ኤርሚያስ ኤርሴሎ ከፓርቲው ራሳቸውን ለማግለል የተገደዱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አምባገነን በመሆናቸው፣ በትክክል የፓርቲውን ሥራ ሊሠሩ ባለመቻላቸውና ኢሕአዴግ ለፓርቲው ሥራ ማስፈጸሚያ የሰጠውን ገንዘብ ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር ለፓርቲው አበድሬያለሁ›› በማለት ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት በማሳወቃቸው ምክንያት መሆኑን፣ አመራሮቹ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡  Ethiopia Raeie Party logo
የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ለፓርቲው ሥራ አመራር ያስተላለፈውን አደራና የፖለቲካ ኃላፊነት ፕሬዚዳንቱ በኅብረት እንዲመራ ከማድረግ ይልቅ መሰናክል መሆናቸውን የሚናገሩት አመራሮቹ፣ ፕሬዚዳንቱ እየፈጸሙ ያሉትን ሕገወጥ ተግባር በማጋለጥ ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለልን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን በመግለጫቸው አካተዋል፡፡ 
አንድ ፓርቲ በመሠረታዊነት የአባላቱን ጥቅምና ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅና በሕዝብ የሚሰጠውን ሥልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጋዊ መነሻ ይዞ መታገል ቢሆንም፣ የኢራፓ ፕሬዚዳንት ለሕዝብ ጥቅም ከመቆም ይልቅ፣ ግለሰባዊ ጥቅም በማስጠበቅ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ስላሠጋቸው የለፉለትን ፓርቲ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ 
አምባገነናዊ የጠቅላይነት አሠራርን መከተል የሚያስከትለውን አደጋ ከወዲሁ መገመት መቻላቸውን የሚናገሩት ከፍተኛ አመራሮቹ፣ መሠረት ያስያዙትንና የለፉለትን ፓርቲ ጥለው ሊወጡ መገደዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ሁለት ጸሐፊዎች በፕሬዚዳንቱ አምባገነናዊ አመራር ተማረው መልቀቃቸውንም አስታውቀዋል፡፡ 
‹‹ራዕይ ከላይ ተሰጥቶኛል፣ ከሰማይ ወርዶልኛል፣ ኢትዮጵያን ትመራለህ ብሎ መንፈስ ስለነገረኝ ከአሜሪካ መጥቻለሁ…›› በማለት የኢራፓ ፕሬዚዳንት እንደሚናገሩ የሚገልጹት አመራሮቹ የምድሩንና የሰማዩን በመደበላለቅ፣ ፓርቲውን ለከፋ ጉዳት እየዳረጉት መሆኑን የፓርቲው አባላት እንዲያውቁት ማድረጋቸውንም አመራሮቹ በመግለጫው አስረድተዋል፡፡ 
አመራሮቹ እንደገለጹት ኢራፓ በፖለቲካ ፓርቲዎች አገር አቀፍ የጋራ ምክር ቤት አባልነቱ፣ ለፓርቲው ፖለቲካዊ ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች ብቻ እንዲውል ኢሕአዴግ 191,898 ብር ከ35 ሣንቲም የሰጠው ቢሆንም፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ራሳቸው አበዳሪና ተበዳሪ ሆነው ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር አበድሬያለሁ›› በማለት 78,898 ብር ለግላቸው መውሰዳቸውንና ይህ ደግሞ ሕገወጥ መሆኑን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ 
በሰሜን አሜሪካና በሌሎች ቦታዎችም በፓርቲው ስም የሚሰበሰብ የዕርዳታ ገንዘብ ለግል ጥቅም እየዋለ መሆኑን የሚጠቁሙት አመራሮቹ፣ በአጠቃላይ ፓርቲው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካን ለመምራት በማያስችልና በማይመጥን አደረጃጀት፣ ዕውቀትና ክህሎት በሌለው አመራር እየተመራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የፓርቲን ስም፣ ማሕተምና ሠርተፊኬት ስለተያዘ ብቻ የፓርቲውን አሠራር አንድ ግለሰብ አጠቃሎ ሊይዝ ስለማይገባ በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመሥርተው፣ እውነተኛ ፖለቲካ ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት በመወሰን ከኢራፓ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም እንዲገነዘበው ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ራሳቸውን ከፓርቲው እንዳገለሉ በመግለጽ የሆነ ያልሆነውን በመናገር የእሳቸውን ስም ሆን ብለው ከማጥፋት የዘለለ እውነታ እንደሌለውና አመራሮቹ የሚሉት ሁሉ ሐሰት መሆኑን በማስረጃ እንደሚያረጋግጡ፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ወልደ ኃዋርያት በፈጸሙት የዲስፒሊን ግድፈት ምክንያት መታገዳቸውን የገለጹት አቶ ተሻለ፣ ከአቶ ኤርሚያስና አቶ ተስፋዬ በስተቀር ሌሎቹ ከፓርቲው ጋር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተሾመ ከሥራ አመራሩ ዕውቅና ውጪ ለሪፖርተር መግለጫ በመስጠታቸው እንዲያብራሩ ሲጠሩ ባለመቅረባቸው፣ ከስምንት ሥራ አመራር ኮሚቴ ውስጥ በስድስቱ ሙሉ ድምፅ መታገዳቸውን ደግመው አስረድተዋል፡፡ 
ከኢሕአዴግ የተሰጠውን ገንዘብ በሚመለከት አቶ ተሾመ ስምንት ሺሕ ብር መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ተሻለ፣ እሳቸው ግን ላለፉት ስድስት ዓመታት አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለፓርቲው ማውጣታቸውን ከማሳወቅ ባለፈ፣ ምንም የወሰዱት ገንዘብ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ የተሰጠው ገንዘብ ከቤት ኪራይ፣ ከሠራተኛ ደመወዝ፣ ከስብሰባና ከተለያዩ ወጪዎች የሚያልፍ ባለመሆኑ የተባለው ሁሉ ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማሙሸት የሚባሉት አባል አመራር አለመሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ፓርቲን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር መቻል አምባገነን ሊያስብል እንደማይችልም አክለዋል፡፡ 
———

‘የሌላ ፓርቲ አባላት በተለያየ ዘዴና ሴራ መውሰድ አስነዋሪ ነው’ – ብርሃኑ በርሔ የዓረና ሊቀመንበር

የዓረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት (ዓረና) ፓርቲን በመልቀቅ ወደአንድነት ፓርቲ ገብተዋል በተባሉ አመራሮችና አባላት ጉዳይ ጋር በተያያዘ የዓረናን ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ በርሄን ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ በጹሑፍ ሰጥተዋል።
ሰንደቅ፡- ሰሞኑን ከአረና ፓርቲ 8 አመራሮችን ጨምሮ 27 አባላት ወደ አንድነት ፓርቲ መቀላቀላቸው እየተነገረ ነው። ይህን ያህል ሰዎችበአንዴ ለመልቀቅ የተገደዱትምንችግርቢኖርነው?
አቶ ብርሃኑ፡-ስምንት/8/ የዓረና አመራሮችና 27 የዓረና አባላት ሰሞኑን በአንዴ ከዓረና ለቀው ወደ አንድነት ፓርቲ አልተቀላቀሉም። የአንድነት ተወካይ በመሆን መቐለ ድረስ የመጡት አቶ አስራት አብርሃም አሉት የሚል የሰማሁት አቶ አስገደ ገ/ስላሴ 27 አባላት አዘጋጅቼአለሁ ብሎን ነበር፤ እንደተባለው ግን አልተገኙም የሚል ነው። ተገኙ የተባሉት 8 ናቸው። እነሱም ሆነ ተብሎ የዓረና አመራርና አባል እየፈረሰ ነው የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ያልነበራቸውን ኃላፊነት ሁሉ ተለጥፎባቸው በተለያየ የማሕበረሰብ ሚድያ አይተናቸዋል። ከአዲስ አበባ ከመጡት የአንድነት 3 ልኡካንን ጨምሮ የተሰበሰቡ 11 ናቸው። ምናልባት በመቐለ የሚገኙት 3 የአንድነት አባላት ጨምሮ ከ 14 ሰው የማይበልጥ መሰብሰቡን ነው የምናውቀው። ስለዚህ 27 የዓረና አባላት ወደ አንድነት ለመቀላቀል አልተሰበሰቡም። አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ለሚያውቁአቸው አባላትና አመራሮች የዓረና አባላትና አመራሮች ሁሉም ወደ አንድነት እየገቡ ነው፤ አንተ ብቻህን እየቀረህ ነው በማለት የደወሉላቸው እንዳሉና ሪፖርት ያደረጉልኝ 8 የአረና አባላትና አመራሮች አሉ። ስለዚህ በማሕበረሰብ ሚድያ እየተሰራጨ ያለውና በስልክ የተደረገው ውትወታ ተደምሮ ሲታይ የአንድነት ፓርቲን ከለላ በማድረግ ዓረና ፓርቲን በውሸት አሉባልታ የማፍረስ ዘመቻ መፈፀሙን ነው። ስምንት/8/ አመራሮች ወደ ተባሉት ስናይ ደግሞ የተባለው ውሸት ለመሆኑ የእያንዳንዳቸውን ልግለፅልህ Berhanu Berhe - chairman of Arena Tigrai party
1/ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ጳጉሜን 2-3/ 2005 ዓ.ም በተካሄደው በ3ኛው የዓረና ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ ተራ አባል ሆነው በ2005 ዓ.ም ባሳዩት የዲሲፕሊን ችግር በመጨረሻ ከባድ ማስጠንቀቅያ ላይ የነበሩ፣ በሓምሌ 2006 ዓ.ም ባሳዩት የዲስፕሊን ችግር በዓረና ደንብ መሰረት ተከሰው እንዲባረሩ የተወሰነባቸው ስለሆነ የዓረና የአመራር አባል ሆነው ወደ አንድነት የተቀላቀሉ አይደሉም። የተባረሩ አባል ሆነው ወደ አንድነት መቀላቀላቸው ነው ሐቁ።
2/ አቶ ሽሻይ አዘናው የማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠው ቢኖሩም ከተመረጡበት ጊዜ ጀምረው 2006 ዓመት ሙሉ ከድርጅቱ ስራ ራሳቸውን አግልለው መቆየታቸው ሐምሌ 20 ቀን 2006 ዓ.ም በተካሄደው የማእከላዊ ኮሚቴ ተገምግመው ያመኑት ሀቅ ሆኖ በስብሳባው ከተገኙ 20 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በ 18 ጥፋተኛ መሆናቸው ታምኖበት ያሰራጩት ውሸት ባሰራጩት ሚድያ እንዲያስተካክሉ ካልሆነ እንዲባረሩ በማለት በዓረና መተዳደርያ ደንብ መሰረት የተወሰነባቸው እንጂ አሁን የዓረና አመራር ሆነው እያለ ወደ አንድነት የተቀላቀሉ አይደሉም ።
3/ ዘቢብ ተሰማ፡- ከ 2005 ዓ.ም ጀምሮ በዓዲግራት ከተማ የዓረና ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ ሆና እየሰራች እያለ ከዞኑ የፀጥታ ኃይሎች ጋር ጤነኛ ያልሆነ ግንኙነት አላት ተብላ በአካባቢው አባላት ከፍተኛ ትችት ይቀርብባት የነበረች እና ለቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቱ የቤት ኪራይ የተላከ ገንዘብ ለግል ጥቅምዋ አውላለች ተብላ ክስ የቀረበባት እና ከሁለት አመት በላይ ከፓርቲው ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላት እንደአባል የማትታሰብ ናት።
4/ ታደሰ ቢተውልኝ፡- ባሳየው ድክመት በቀላል ማስጠንቀቂያ ተብሎ ራሱ የወጣ ግን ተባረርኩኝ እያለ ራሱ በተለያየ ሚድያ ያወጀ ስለሆነ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልነቱን ተገን አድርጎ ብቻ ወደ አንድነት ተቀላቀለ የሚያስብል አይደለም። ምክንያቱ ከዓረና ከወጣ ወደፈለገው ፓርቲ የመቀላቀል ጉዳይ የራሱ ውሳኔ ነው።
5/ አብደል ወሃብ ቡሸራ፡- በ2ኛ ገባኤ እንጂ በ3ኛ ጉባኤ አመራር አባል ሆነው አልተመረጠም ብቻ ሳይሆን በእድሜና በጤና ምክንያት እንደ ተራ አባልም በስራ ላይ አልነበሩም።
6/ ገብሩ ሳሙኤል፡- የቁጥጥር ኮሚቴ አባል ሆኖ ባሳየው የዲሲፕሊን ችግር እስከሚቀጥለው ጉባኤ ታግዶ እንዲቆይ የተወሰነበት እንጂ የዓረና አመራር ሆኖ ሰሞኑን ከዓረና ለቆ ወደ አንድነት የተቀላቀለ አይደለም።
7/ ይልማ ይኩኖ፡- ራሱ የስንብት ጥያቄ አቅርቦ የስንብት ጥያቄውም ተቀባይነት አግኝቶ ከአመራር ኃላፊነት ውጭ የነበረ ነው።
8/ 8ኛ ሰለሞን የተባለ የአቶ አሰገደ ቤተሰብ ሆኖ ተራ አባል ነው።
ሁኔታው እንዲህ ሆኖ እያለ 20 የማእከላዊ ኮሚቴ አባል በስራ ላይ እያለ ዓረና እየፈረሰ ነው የሚል መልእክት ለማስተላለፍ በመከጀል ብቻ ሰሞኑን ዓረናን ትተው በሰልፍ ወደ አንድነት እንደገቡ ተደርጎ የሚወራው አንድነትን እንደ ዋሻ በመጠቀም የተዘየደ መሰሪ ተግባር ነው።
ሰንደቅ፡-በዓረናውስጥውስጣዊዴሞክራሲመላላት፣ቡድንተኝነትናመከፋፈልመኖሩይነገራል፤ይህእውነትነው?
አቶ ብርሃኑ፡-እጅግ በጣም ውሸት ነው። ውስጣዊ ዴሞክራሲ መላላት ማለት በፓርቲው ደንብ አለመገዛት ወይም የፓርቲው ደንብ ባለማክበር የአባላት መብቶች መጣስ ሲደጋገምና አስፈላጊውን እርምት ለማድረግ አለመቻል የሚገልፅ ይመስለኛል። በዓረና ውስጥ የአባላት መብት የተከበረና አሳታፊ ሂደት አለ። አመራሩም በደንቡ በተደነገገው መሰረት ይሰበሳባል፤ ሪፖርት ለበላይ አካሉ ያቀርባል። ኃላፊነትና ተጠያቂነት አስማምተን እንሰራለን። የፓርቲው የአባላት ጥራት ካልተጠበቀ ተልእኮአችን በሚገባ መፈፀም እንደማይቻለን ተገንዝበን ለፓርቲው ባእድ የሆኑ ሰዎች ሰርገው ሲገቡ ወይም በሂደት ለፓርቲው ባእድ መሆን ሲጀምሩ የፓርቲያችን ጥራት መጠበቅ ግዴታችን ስለሆነ በህገደንባችን መሰረት የፓርቲያችን ደህንነት እንዲከበር ተግተን እንሰራለን። ባለንበት አስቸጋሪ የክልላችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ችግሮች ተጠቅመን በሰላማዊ የትግል ስትራቴጂ ራእያችን እውን ማድረግ የምንችለው የዓረና አባላት የሰላማዊ ትግል ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚያስችለን በጠንካራ የፓርቲ ዲሲፕሊን ካልተገራን ለውጤት እንደማንበቃ የተገነዘብነው ነው። ከተመሰረትንበት ቀን ጀምሮ እስከ አሁን ስዓት ገዢው ፓርቲ ሊያዳክመን ብቻ ሳይሆን ጭራሹን ሊያፈርሰን በሙሉ አቅሙ እየሰራ በሃገር ደረጃ ተስፋ የሚጣልብን ፓርቲ ለመሆን የቻልነው በጠንካራ የፓርቲ ዲሲፒሊን እየተመራን ለአንድ አላማ በጋራ ለመስራት በመቻላችንና ችግር ሲያጋጥመንም በጊዜው ለማስታገስ የሚያስችለን የፖለቲካ ጥንካሬ በማረጋገጣችን ነው። የዓረና አመራርና አባላቱ እየተናበቡ የሚሄዱ ውሁድ አካሎች ሆነዋል። ይህ የፈጠርነው ውስጣዊ ፖለቲካዊ ጥንካሬ በውስጥ ሊቦረቡሩን ለሚፈልጉም እንደማይሆንላቸው ተረድተው በፓርቲው መድረክ ምንም ሳይተነፍሱ ሹልክ ብለው በጋዜጣና በፌስቡክ አካኪ ዘራፍ እንዲሉ ያስገደዳቸው ይመስለኛል። ፓርቲው ካልፈለጉት በጨዋ አንደበት መተው እየቻሉ የተሰጣቸው ተልእኮ ፈፀምን ለማለት የፈሪ ዱላቸውን ይወረውሩብናል።
የዓረና አመራር በጥቂት ጎልማሶችና በብዙ ወጣት አመራሮች የተሞላ ሆኖ ዓረና ከተመሰረተ ጀምሮ እጅግ ተግባብቶ የሚሰራ አመራር ያለው ነው። የዲሲፕሊን ጉድለት የታየባቸው አባላትም ሆነ የአመራር አባላት በግልፅ መድረክ ተገምግመው ለቀረበባቸው ሂስ የመከላከል መብታቸው ተከብሮ ለአላማቸው ይደግፍልናል የሚሉት ማስረጃ የማቅረብ መብታቸው የተከበረ ነው። አንዳንድ የአመራር አባል የነበሩ በፓርቲው ውስጥ አንዳች የተለየ አቋም ሳያሳዩ፣ ፓርቲው ተወያይቶ ውሳኔ እንዲሰጥበት አጀንዳ ሳያስይዙ በማህበረሰብ ሚድያና በጋዜጣ ያውጃሉ። የፓርቲው መዋቅሮች በመተው በጋዜጣ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ከሁለት ችግር ይመነጫል። አንደኛውና ዋናው ሆነ ተብሎ ፓርቲውን ለማጥላላት ድጋፉን ለመገደብ የሚከጀል ሴራ አልያም በፓርቲው ውስጥ በአባላትና በአመራሩ ሊደመጥ የሚችል አጀንዳ አለመኖርንና በራስ ካለመተማመን የተነሳ ድክመትን ለመሸፈን የተደረገ ይሆናል።
የዓረና ጠቅላላ ጉባዔ የሊቀመንበሩ ቡድን ተባለ፣ የዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ የሊቀመንበሩ ቡድን ተባለ፣ ሥራ አስፈፃሚው የቁጥጥር ኮሚቴው ጭምር የሊቀመንበሩ ቡድን ተባለ፤ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሊቀመንበሩ በእነዚህ የፓርቲው አካላት ተደማጭነትና ተሰሚነት ካለው ማለት የሚቻለው ሊቀመንበሩ በፓርቲው ተቀባይነት አለው ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ከሥራ ውጤት እንጂ ከውሸትና ከአሉባልታ ሊገኝ አይችልም። ቡድናዊነት አለ፤ ውስጣዊ ዴሞክራሲ የላላ ነው በማለት የሚጮሁቱ እየዋሹ እንደሆነ ጥቂት አብነቶች ልጥቀስ።
የእነ አቶ አስራት አብርሃምና አቶ ጉዕሽ ገ/ፃድቅ ከዓረና መልቀቅ ምንም ምክንያት የሌለው ነው በማለት በፓርቲው ቁጥጥር ኮምቴ በፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ በጉባኤ ጭምር እነሱ ራሳቸው የወሰኑት እያለ ተመልሰው በፓርቲው ውስጥ ባለው ችግር እንደወጡ ይለፍፋሉ። ከዚህ ባለፈ በተለይ በአቶ ጉዕሽ ገብረፃድቅ ከደህንነት ባለው ንክኪ እንደወጣ መምህር ታደሰ ቢተውልኝ በምርጫ 2002 ዓ.ም የነበረው ንክኪና ወደ አዲስ አበባ በሥራ እንደተቀየረ የጠበቀው መልካም ሥራና ሽልማቶች በመጥቀስ ይህንኑ ሳታሳወቁን ቆያችሁ በማለት አሁን ዓረና ያለን አመራሮች ወቅሰውን ነበረ። አሁን ተመልሰው በቡድናዊነት ወጡ ብለው ለመናገር መዳዳታቸው ችግሩ ሌላ መሆኑን ያመለክታል።
አቶ አስገደ ገብረስላሴ በ3ኛው ገባኤ በእኔው በዛ ጉባኤ ሊቀመንበር የሆንኩት ሲተች ሃሳቤን አይቀበለኝም፣ ይንቀኛል፣ እንደ ሰው አያየኝም፣ ፀረ ዴሞክራት ነው የሚል ነበር። ሆኖም ግባ ባልከው ስራ ሁሉ የሚሰራ ነው ነበር ያለው። ያለውን ልደግምለት ፈልጌ እንጂ የተናገረው ነገር በጉባኤውም ሆነ በተመረጠው አዲስ ማእከላዊ ኮሚቴ ተቀባይነት እንዳልነበረው ምርጫው መስክሮአል። በማእከላዊ ኮሚቴ ቢመረጥ አልቃወመውም ነበር ያለው። ወዲያው ተገልብጦ ደግሞ አሁን ህወሓት ነው እያለ ያቅራራል።
አቶ አስገደ ገብረስላሴ በ 2005 ዓ.ም መጨረሻ ላይ በፓርቲው የቁጥጥር ኮሚቴ ከፋፋይ ቡድናዊ ተግባር በመፈፀምና የአመራሩን ስም ሆነ ብሎ ማጥፋት በሚል የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ሲወሰንበት የቁጥጥር አባል በመሆን ከወሰኑት ውስጥ አንዱ ታደሰ ቢተውልኝ የነበረ ሆኖ አሁን ከአቶ አስገደ ጋር በመሆን ቡድናዊነት በማለት የፓርቲውን ስም ያጠፋል። በሃምሌ 2006 ዓ.ም ባካሄድነው የማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እኔን ይሰልለኝ እንደነበረም ያመነበት ነው። እንግዲህ መሰለል ካለ ቡድናዊነቱ እነሱ ጋ መሆን የሚያረጋግጥ ነው።
ሓምሌ 2005 ዓ.ም በተካሄደው 3ኛው ጉባኤ አቶ ታደሰ ቢተውልኝ የጉባኤው አዘጋጅ በመሆን ውክልናው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደተፈፀመ ለጉባኤው ሪፖርት አቅርቦ በጉባኤተኛው ተደግፎ ያለፈ ውሳኔ እያለና አቶ አስገደ ገብረስላሴ፣ አቶ ሽሻይ አዘናው፣ አቶ ገብሩ ሳሙኤል ዴሞክራሲያዊ ውክልና ብለው የወሰኑበት ጉባኤው በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጠቃለሉን በማጠቃለያ ንግግር ሲደመደም ተቃውሞ ያልነበራቸው አሁን ተመልሰው ቡድናዊነት እያሉ ሲባዝኑ እነሱን ለትዝብት የሚዳርጋቸው ነው።
መድረክን ለማዋሃድ በዓረና በኩል የተደረገው ጥረት በአባላት ስብስባ በዝርዝር ቀርቦ በዓረና በኩል የተቻለውን እንደተሰራ አቶ አስገደ ባለበት መግባባት የተደረሰበት እያለና በማእከላዊ ኮሚቴው መደበኛ ስብሰባ በዝርዝር የፅሁፍ ሪፖርት ቀርቦ አቶ ሽሻይ አዘናውና አቶ ታደሰ ቢተውልኝ ባሉበት ጥልቅ ውይይት ተደርጎበት በመጨረሻ እነሱንም ጨምሮ በሙሉ ድምፅ በዓረና በኩል የሚቻለውን ሁሉ ተሰርቶአል በማለት የተወሰነና የወሰኑት እያሉ አሁን የአንድነት በርን አንኳኩተው እንዲከፈትላቸው ለመማፀን ትምክህት ምንትሴ እያሉ ብዙ መቀባጠራቸው በውሸት የተገነባ ዓረናን ለማዳከም የከጀሉት ሴራ ያደርገዋል።
ስለዚህ በእርግጠኝነት በዓረና አመራር ውስጥ ቡድናዊነት የለም። እጅግ በጣም እየተናበበና እየተመካከረ የሚሰራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያጋጥም መናወጥ የመቋቋም ብቃት ያለው አመራር ነው ያለው። አሁን ዓረና ዘርቶ ያፈራውን አጭደው ለመጠቀም የሚፈልጉ ግብዝ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ይህን ጉዳይ የተገነዘቡት ነው። አሁን ወደ አንድነት ገባን በሚሉት ግን ቡድናዊነት መኖሩ እናውቀው ነበር። ከዓረና እንደወጡ በየአካባቢው ያደርጉት የነበረ ቡድናዊ ተግባር ጳጉሜን 2-3 /2005 ዓ.ም በተካሄደው ጉባኤ ቡድን ፈጥረው መግባታቸው ከዓረና እንደወጡ በአባላት ስብሰባ በግልፅ ቀርቧል። ሲገልፁትም አቶ አስገደ እንድንደግፈው ነግሮን እኛም ልንደግፈው ተዘጋጅተን መጥተን በጉባኤው ሁሉም ነገር ፍሬ አልባ ሆኖ አገኘነው በማለት ገልፀውታል። በ3ኛው ጉባኤ እነአቶ አስገደ ጉባኤው የብቻቸው እስኪመስል ድረስና ጉባኤተኛውም እኪሰለቸው ሀሳባቸውን ገልፀዋል። በአቶ አስገደ ሀሳብ ጉባኤተኛው መሰላቸቱ በገባኤው አዳራሽ በግልፅ ተናግሮአል። አቶ አስገደ በራሱ ደካማ ሃሳብ በጉባኤው አባላት ተቀባይነት ማጣቱን እንዳወቀ ወጣቶች እንዲተኩኝ ከመመረጥ ራሴን አግልያለሁ አለ።
በዓረና ማእከላዊ ኮሚቴ ያለ በድምፅ መሳተፍ አለብኝ በማለት መማፀን ጀመረ። ከመተዳደርያው ደንብ ውጭ በመድረክ ስብሰባ አሳትፉኝ በማለት ይማፀነን ነበር። ወጣቶቹ ኃላፊነቱን ተረክበው ሲሰሩ ደግሞ ዓረና ካላፈረስኩ በሚል አሉባልታን እንደ መሳርያ በመጠቀም ዘመቻው ተያያዘው። በዓረና ውስጥ ሆኖ አልሆንለት ሲለው አሁን ደግሞ መልኩን ቀይሮ መጣ። ዓረና በትግራይ የተያዘው ሰፊ ህዝብን ማእከል ያደረግ የፖለቲካ ስራ ለማደናቀፍ አስቸካይ ጉባኤ ይካሄድ፣ ለጉባኤው ማስፈፀሚያ ስፖንሰር አግኝተናል በማለት መበጥበጥ ጀመሩ፣ ጥያቄአችሁ በዓረና ደንብ መሰረት ብቻ ነው የሚስተናገደው ሲባሉ ማንገራገር ሆነ ስራቸው። ከሃምሌ 19-21/2006 ዓ.ም በተካሄደው የማእከላዊ ኮሚቴው መደበኛ ስብሰባ የአባልነት መብታችሁን መሠረት በማድረግ ጥያቄ አቅርባችሁ ታፈንን በማለት በዓለም አለ በተባለ ሚድያ ሁሉ ዓረናን ለማጥላላት የዘመታችሁ የትኛው የዓረና ደንብ ድንጋጌ ነው የተጣሰው ሲባሉ ጭራሽኑ ማስረዳት አልቻሉም።
ሰንደቅ፡-የተፈጠሩአለመግባባቶችንበውይይትመፍታትያልተቻለውለምንድነው?
አቶ ብርሃኑ፡-የልዩነቱ ባህሪና ልዩነት የፈጠሩ ሰዎች ፍላጎት ነው የሚወስነው። የልዩነት መፍቻ መንገድ ውይይት ነው፣ ውይይቱም በግልፅና በሚያሳምን መረጃ ተደግፎ ሲንሸራሸርና ማጠቃለያ ውሳኔው በተሰበሰበው ሲዳኝ ነው። አንዳንዶቹ አቶ አስራት አብርሃ ወደ አንድነት ሲቀላቀል በስውር የተቀላቀሉ ናቸው። ዓረና ውስጥ የቆዩት የዓረና አባላትን አባብለው ለመውሰድ ነበር። እንደተመኙት ሳይሆንላቸው እየገለፁት ያለውም ያ ምኞታቸውን ነው። ሌላ ታሳቢ የሚሆነው ደግሞ የታለመው ፍላጎት አልሳካ ሲል መነሻው አለመግባባት ሳይሆን አውቆ አጥፊነትና የተደበቀ ፍላጐት ስለሚሆን መግባባት በአሉባልታ ብሎም እስከ ፓርቲውን የማፍረስ እንቅስቃሴም ይሄዳል። በተደጋጋሚ የሚያጋጥመን እሱ ነው። ጉባኤ በመጣ ቁጥር ቁልፍ የፓርቲው ሃላፊነት ለመያዝ ከባእድ ሃይሎች ይዘጋጃሉ። የፈለጉት አልሳካ ሲል ፀረ ፓርቲው እንቅስቃሴዎች ይዘጋጃሉ የፓርቲው እንቅስቃሴ ለመገደብ። ስለዚህ የልዩነቶቹ ምንጭ ፓርቲውን ከማሳደግ አጀንዳ የተያያዙ ስለማይሆኑ ነው።
ሰንደቅ፡-የሰዎቹመልቀቅበፓርቲውላይየሚያሳድረውአሉታዊተጽእኖውእምንድረስነው?
አቶ ብርሃኑ፡-መግባትና መልቀቅ ያለ ቢሆንም ከአረና የለቀቁት በዓረና ላይ የሚኖረው ተፅእኖ በምክንያታቸው መጠን ብቃት ባይኖረውም እነሱን በመደገፍ አሉባልታውን በማስፋፋት መጠን ሊታይ የሚችል ነው። ከመልቀቅ ጋራ በተያያዘ ከተፅእኖው በፊት ለመልቀቅ ምንጭ የሆነው ከአጠቃላይ የክልሉ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የሚታይ ነው። ገዢው ፓርቲ ህወሓት ዓረናን የሚያየው በክልል ፓርቲነቱ ሳይሆን ህወሓት /ኢህአዴግን የሚያጠፋ ጠላት ከመሃል አገር የምናሰባስብ አድርጎ ነው። ለምሳሌ ግንቦት 20/2006 ዓ.ም የወጣው የህወሓት ልሳን የሆነው የወይን መፅሄት ልዩ እትም ከጅምሩ እስከመጨረሻው ስለ ዓረና የሚያጥላላው በፖለቲካ አምዱ የሰፈረው በዋና ርእሱ “ንስኹም ተመን እረዩ ቐታሊና ንሕና ዕንፀይቲ ክንአሪ መድረሪና” ትርጉሙ “እናንተ እኛን የሚያጠፋ እባብ አሰባስቡ፤ እኛ እንጨት እንሰበስባለን የምግባችን መስሪያ” በማለት የሚያስብ የመንግስት ስልጣን የያዘ ገዢ ፓርቲ በዓረና ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን ጫና ማሰቡ የሚከብድ አይደለም።
በሌላ መልኩ ደግሞ ኢትዮጵያ እየገዛ ያለው የትግራዩ ህወሓት ብቻ እንደሆነ የሚያስቡና ህወሓትን ማሸነፍ የቸገራቸው ዓረና በትግራይ በሚሰራው የፖለቲካ ስራ በህዝቡ የታዩት የለውጥ ፍላጎት እየተጠናከረ መምጣት ለፍላጎታቸው መጠቀሚያ በማሰብ የዓረና የስራ ውጤቶች ለመቀማት የሚያስቡ አሉ። የመጀመርያው ስህተት ኢትዮጵያን እየገዛ ያለው አህአደግ እንጂ ህወሓት ብቻ አይደለም። ግዙፉ የፖለቲካ ስህተት አህአዴግ በሃገር ደረጃ በምርጫ ካልተሸነፈ ህወሓት ብቻውን ቢሸነፍም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንደማይመጣ አለመገንዘብ ነው። ይህ ስህተት ደግሞ ሌላ ስህተት እየወለደ ለኛ ለዓረናም ተረፈን። ፍላጎታቸው ለማሟላት ደግሞ በዓረና ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሮ ወደ ፓርቲያቸው የሚቀላቀሉ ሰዎች ለመቃረም የሚጠባበቁም አልታጡም። እነሱም የአንድነት አባቶች ተመስለው የዓረና ፓርቲን ውህደት ፈላጊና ውህደት የማይፈልግ በማለት መከፋፈልን ለማጠናከር የሚሰሩ አሉ። ይህ ችግር በሃገር ውስጥም በውጭም የሚስተዋል ሆኖ ይህንኑ ለሚያስፈፅሙላቸው የሚተባበሩ አልታጡም። አስቸኳይ ጉባኤ ይካሄድ ስፖንሰር አግኝተናል በማለት በድፍረት የገንዘብ ችግር የለብንም እየተባለ የዓረና አባላትን መደለል የተጀመረውም መነሻው ከዚህ ነው። ይህንኑ እኩይ ፕሮጀክት አያሰሩንም የተባልነው ደግሞ የህወሓት ባንዳ በማለት ተለጠፈብን። በፓርቲው አለመተማመንና መጠራጠር ነግሶ ያሰቡትን ለማሳካት በዓረና ሊቀመንበር የያዙትን ሁሉ መተኮስ ጀመሩ፤ ህወሓት ነው በማለት። ግን ከተራው አባል ጀምሮ እንዳሰቡት ለሆዱ የሚያድር ሆኖ ስላልተገኘ ቅንጣት ድጋፍ ሳያገኙ ቀርተዋል።
ህወሓትም ይህንኑ መልካም አጋጣሚ የሆነለት በመጠቀም በማሰር፣ በመደብደብ፣ በመሰለል፣ በማጥላላት፣ ዓረና የጀመረው የተጋ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማፈን ስራዬ ብሎ አጠናክሮ ቀጠለበት። የህወሓት/ኢህአዴግ የፖለቲካ እስትንፋስ በአቶ መለስ ዜናዊ ዝና ላይ እንደቆመች የሚያምነው ህወሓትም በዓረና ሊቀመንበር ላይ በፀረ መለስነት ፕሮፓጋንዳ ተያያዘው። የዓረና ሊቀመንበር “የመለስ ራዕይ የጥፋት ራዕይ ነው ማለቱ ለትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለ80 ሚልዮን የኢትዮጵያ ህዝብ መሳደቡ ነው” በማለት። ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ከተለያየ ፍላጎት ግን ዓረናን ለማዳከም ብሎም ለማፍረስና ከፍርስራሹ ምናምን ለመልቀም በሦስት አቅጣጫ የተዘመተብን እንቅፋት ስንቋቋም የዚህ ዘርፈ ብዙ ሴራ ጉዳይ አስፈፃሚዎችም ልክ እንደየዘርፉ ቢለያዩም ዓረናን በመፈታተን ግን አንድ ሆኑ።
የተፈጠረው ተፅእኖ በሁለት መልኩ የሚታይ ነው። አንደኛው ከአጭር ጊዜ አኳያ ጥርጣሬ ሊጭር መቻሉ፤ በሌላ መንገድ ደግሞ አሉባልታው ውሸት ነውና ግልጥልጡን ሲወጣ የዓረና ፓርቲ ጥንካሬና የበቃ አመራር ጎልቶ እንዲወጣ የማድረግ ሚናም ይኖረዋል። በአባላቶቻችን የሚያሰጋን የለም። በውጭ የድጋፍ ኮሚቴዎቻችን ከሚገባ በላይ የዓረና ጥንካሬ ጎልቶ እንዲወጣ መደረጉና ዓረናና የድጋፍ ኮሚቴዎቹ በቅርብ በመመካካር ከነበረው የበለጠ ድጋፍ ፈጥሮልናል። ይህ አቶ አስገደም ያወቀው ነው። የዓረና የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረቅ በአቶ አስገደና በህወሓት የተቀናጀ ዘመቻ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። በአንድ ወገን በምርጫ ዋዜማ አላስፈላጊ መነታረክ አያስፈልግም፤ የፈለገው ችግር ቢኖር መቻቻል ባሰፈለገ የሚሉ አሉ። በሌላ ወገን በተለይ የተባረሩትን ሰዎች ባህሪ የሚያውቁ ለፓርቲው ጤንነት ነው የሚሉ አሉ። ህወሓት ደግሞ ዓረና ፈርሷል እያለ ሳንፈርስና ፈርሰናል ሳንል በራሳቸው የፈረሱት በህወሓት ያመካኛሉ በማለት ያወራሉ። ይህ ሁኔታ በውስጥ የፓርቲ አመራርና የአባላቶቻችን ጥንካሬ የጨመረ ነው። የማእከላዊ ኮሚቴው ሪፖርትና ውሳኔ አባላቶቹ እንዲወያዩበት ተደርጓል። በዛ መሠረት መተማመን ተፈጥሮአል። ይህ ማለት ግን ካለንበት የክልላችን ፈተናዎች አንፃር ሙሉ በሙሉ ከሰርጎ ገቦች ነፃ ነን ብዬ ለመማል አልደፍርም። በማእከላዊ ኮሚቴው ሪፖርትም የተሰመረበት ጉዳይ የአባላት ጥራት በተመለከተ አተኩረን መስራት እንዳለብን ነው። ፓርቲው አደጋ የሚጥል ውስጣዊ ችግር የሌለ መሆኑ ግን በእርግጠኝነት መናገር እደፍራለሁ። ዓረና የእነ አቶ አስገደ የተለመደ አሉባልታና የህወሓት የሽብር ፖለቲካ መክቶ በ2007ዓ.ም ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ መቅረቡ አይቀሬ ነው። ፖሊሲውን የማስተዋወቅ ሥራም አጠናክሮ የሚቀጥልበት ይሆናል።
ሰንደቅ፡- ከአረናወጥቶወደ ሌላፓርቲመግባትከፓርቲዲሲፕሊንአኳያእንዴትያዩታል?
አቶ ብርሃኑ፡-ዓረና አልተመቸኝም ያለ የመተው መብት አለው። ዓረናን ከተወ በኋላ በመሰለው ፓርቲ አባል ሊሆን ይችላል። አስነዋሪ የሚሆነው ግን በገዛ ራስ ጥረት አባላትን መፍጠር ሲቻል የሌላ ፓርቲ አባላት በተለያየ ዘዴና ሴራ ለመውሰድ መሞከር ነው። ዓረናን በችግር እንደተጠመደና አባላቶቹም እየወጡ እንደሆኑ በማስመሰል የገዛ ራስ ፓርቲ በማሞካሸት የሚሰራ ስራ በእኔ እምነት እጅግ ግብዝና ዘላቂነት የሌለው ፖለቲካ ነው። ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ እየተገለባበጡ መዞር ደግሞ ብዙ መዘዝ ያለበት እንደሆነ እናውቃለን። ከደህንነት በፈጠሩት ግንኙነት ዓረናን ለማወክ ሲሰሩ ዓረና ጥጋቸውን እንዲይዙ በማድረግ ጥራቱን ጠብቆ ሲጓዝ ሰዎቹ በአንድነት የክብር አቀባበል ተደርጎላቸው እንዳወቅን አንድነቶች እንዲጠነቀቁ ነበር የመከርነው። ከአንድነት ወጥተው ደግሞ በመኢአድ ሲንሸራሸሩ እየታዘብን ነው። በ2005 ዓ.ም በአንድነት የተመዘገቡ ወደ ዓረና እንመለሳለን እንዳሉን አብረን የምንሰራ ስለሆን በዓረና መሆንና በአንድነት መሆን ልዩነት የለውም ብለን ነበር ያላስተናገድናቸው። አብረን እንስራ እያሉ አብረውት በሚሰሩ ፓርቲ የሚበጠብጡ ተቀብሎ በክብር አስተናገድናቸው። እንኳን ደህና መጣችሁ የሚለው በሌላ አነጋገር አብረን እንስራ ማለቱ የሚጎዳ ነው የሚሆነው። ግለሰቦች በፈለጉት ፓርቲ የመግባት መብት አላቸው። ፓርቲዎችም የውስጥ ጥራታቸውን የሚጎዳና የትብብር ስራቸው የሚጎዳ ሆኖ ሲያገኙት ያለማስተናገድ መብቱ አላቸው።
ሰንደቅ፡- አረናከአንድነትፓርቲጋርየመዋሃድሃሳብነበረው፤ ጉዳዩከምንደረሰ?
አቶ ብርሃኑ፡-የትም አልደረሰም። መወሃድ ይቅርና ተባብሮ ለመስራት የሚያበላሹ ምልክቶች እየታዩ ነው። አንድነት እርምት ካልወሰደባቸው የችግር ምንጭ የሚሆኑ ይመስለኛል። ይህን ጉዳይ ከአንድነት ሊቀመንበርም ጋር ተነጋግረንበታል።
ምንጭ፡- ሰንደቅ፣ መስከረም 21፣ 2007

ያለ ብሔራዊ መዝሙርም፣ ያለ ሰንደቅ ዓላማም ኖረን አናውቅም



ኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር ለመጀመሪያ ጊዜ ያስዘመረችው በንጉሱ ዘመን ነው። በንጉስ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን ሦስት መዝሙሮች ነበሩ። «ኢትዮጵያ ሆይ (ብሄራዊ መዝሙር) ደሙን ያፈሰሰ (ጠዋት ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል በተማሪዎች የሚዘመር) ተጣማጅ አርበኛ (ምሽት ባንዲራ ሲወርድ በተማሪዎች የሚዘመር) »
በንጉሱ ጊዜ የነበረው ብሔራዊ መዝሙር አዝማች ይህን ይመስላል።
«ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ
በአምላክሽ ኃይል በንጉስሽ
ድል አድራጊው ንጉሳችን
ይኖራሉ ለክብራችን»
መዝሙሩ .. 1930 እስከ 1974 ድረስ ባሉት 44 ዓመታት ተዘምሯል። ግጥሙ የወል የሚባል ባይሆንም በጋራ የተሰራ ነው፣ ዜማውም አርመናዊ ዜግነት ባለው ኢትዮጵያዊ ነዋሪ ኬቮክ ናልባንዲያን .. 1926 የተቀመረ ነው ሲባል ሰምቻለሁ።
በንጉሱ ዘመን የነበረውን መዝሙር ደርግ ስልጣን ሲይዝ ቀየረው የኢትዮጵያን ጭቁን ህዝቦች የማይወክል፣ የንጉሱንና የሰሎሞናዊውን ስርወ መንግሥት የበላይነት የሚሰብክ ነው በሚል። ከዚያም እሱም እንዲሁ የወቅቱ ወካይ ነው ያለውን ብሄራዊ መዝሙር አወጀ።
«ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በህብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ…»
ይህ መዝሙርም .. 1975 እስከ 1992 ድረስ ተዘምሯል። አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ የግጥሙ ደራሲ፣ ዳንኤል ዮናስ ሃጎስ የዜማው አቀናባሪ ናቸው።
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ሀገሪቱን በሽግግር መንግሥት መምራት ከጀመረ ባሉት የአንድ ዓመት ጊዜያት ኢትዮጵያ መዝሙር አልነበራትምን? ካልን አዲስ መዝሙር አልነበራትም። በዚህም ምክንያት የቀደመው መዝሙር ተግባራዊ ሆኗል። ይህ ጊዜ ከግንቦት 20/1983 እስከ ሐምሌ 2/ 1984 / ድረስ ያለው ነው።
«የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ
ታየ ህዝባዊነት ዳር እስከዳር በርቶ…»
መዝሙሩ ሐምሌ 2/1984 ይፋ ሆነ፤ የግጥሙ ደራሲ ደረጀ መላኩ፣ የዜማው አቀናባሪ ሰለሞን ሉሉ ናቸው። ኢትዮጵያ 1 ዓመት ያለአዲስ መዝሙር ብትኖርም፣ ያለ ሰንደቅ ዓላማ ግን አልኖረችም። ሰንደቅ ዓላማዋ እንደተውለበለበ፣ ኢትዮጵያዊ ነታችንን እንደገለፀ ይኸው እስካሁን አለን፤ ሰኞ በጋራ ሰንደቃችንን ከፍ እናደርጋለን፣ ሀገርም ውስጥ ውጭም ያለን በልባችንም በተግባርም ከሰንደቅ ዓላማችን ጋር አገራችንን እናስብ። ክብር ለሰንደቅ ዓላማችንና ለክብሩ ለቆሙ ሁሉ ይሁን!!ግን አንድ ጥያቄ ልጠይቅ፣ አንወሻሽና እርስዎ የትኛውን መዝሙር ዘምረዋል?
ይህን እያሰብን በሦስቱ መዝሙሮች ላይ አጠር ያለ ሂሳዊ ቅኝት እናድርግ። ሂሱ ከገጣሚዎቹ አተያይ ጋር አይዛመድም፣ ብቻ እንደ አንባቢ ወይም መዝሙር ሰሚ ለማለት ነው።
የዚህን ጽሑፍ መነሻ አሁን እየተዘመረ ያለውን «የዜግነት ክብር» አድርገን መዝሙሩ ከርዕዮተ ዓለም አንፃር ምን መልዕክት ያስተላልፋል በሚል እንቃኝ፤ ኋለኞቹንም ለማንፀሪያነት እንጠቀም።
ምሁራን የርዕዮተ ዓለም ማደሪያው ቴክስት(text) ነው ይላሉ፤ ቴክስት ስንል እንደ ጉዳይ ማደሪያ ሰው ሊሆንም ይችላል። ጉዳይ ደግሞ በዚህ ጽሑፍ ቅኝት አንፃር ርዕዮተ ዓለም የተቀነቀነበት መዝሙር ነው ማለት ነው።
“Ideology resides in texts, especially in the meaning of texts. Texts are open to all kinds of interpretations associated with other text” – Silan Li V1-347.
“Fiction are not fixed and immutable entities, for they are always open to ideological manipulation” – de Man 1990:183.
ርዕዮተ ዓለም ለተለያዩ ትርጓሜዎች በስፋት የተጋለጠ ነው፡፡ ከደራሲው ፍላጎት ውጪ አንባቢው ወይም ተደራሲው ባሻው መልክ ቢረዳው ስህተት የለበትም፡፡
በሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ውስጥ የሚፈጠር ርዕዮተ ዓለም ከአንድ ማህበረሰብ (ማህበረ መሰረት) ውስጥ የሚመነጭና የሚገኝ ነው። ርዕዮተ ዓለም የአንድን ማህበረሰብ ወይም ህዝብ ፍላጎት አጠቃልሎ የመያዝና የመጠበቅ ባህሪ አለው። የዚሁ ቃል ፈጣሪ ጀርመናዊው «ዴስቱስ ትረስ» ይህን ጨምሮ አንድ ታሪክ በራሱ የርዕዮተ ዓለም መገለጫ መሆኑን ይነግረናል።
ርዕዮተ ዓለም እንደ ሀሰተኛ ማነቃቂያ ይወሰድ የነበረና በስልጣን ላይ ያለውን ወገን አይነኬነት ለማቆየት አስተዋጽኦ እንደነበረው ደግሞ ማርክሳዊ ንድፈ ሃሳብ ያመለክተናል። ሆኖም በርካታ ምሁራን ይህን አስተሳሰብና ትርጓሜ ስህተት መሆኑን ነቅፈው ተችተውታል። ለምሳሌ እንደ ፖል ዲማን፣ ፒተር ስሎተርጂክ፣ ዴኒስ ተርነር፣ ራይሞንድ ገስ፣ ቴሪ ኢግላተን እና ፍሬዴሪክ ጀምስ ያሉ።
ፈረንሳዊው ፈላስፋ ሉዊስ ኦልትሰርም ርዕዮተ ዓለም ሰዎች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ እንዲሆንላቸው የሚመኙትንና የሚፈልጉትን የሚገልፁበት ነው ይለናል። ኢግላተን በበኩሉ የርዕዮተ ዓለም ትርጓሜ ይሆናል ብሎ 16 ፍቺዎችን አስቀምጧል። ከዚህ ውስጥ ርዕዮተ ዓለም እንደ ሥነ ጽሑፍ ከነባራዊ ሁኔታ (ጊዜና ቦታ) ሊነጠል የማይቻል ነው በሚል ይገልፃል።
የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ግጥም በቀላል ወይም ተነባቢ ቃላት የተዋቀረ ነው፤ ሆኖም የግጥሙ ሃሳብ ጥልቅና ታሪክ ተኮር ነው። ለዛሬው ንግርት የኋላውን ይታከካል፤ የኋላው ጊዜ ዘመን ጥሩ እንዳልነበር እያስታወሰ ዘመን ፈፅሞ እንደማይመጣ አስረግጦ ይናገራል።
አሁን የተገኘችው ሀገር በአደራ የተረከብናት መሆኑን እያመላከተና ሀገር ከሌለ ህዝብ እንደማይኖር እየነገረ ኢትዮጵያዊነትና ህዝባዊነት ፈፅሞ እንደማይነጣጠሉ ያስገነዝበናል። የመጪውን ጊዜ ብሩህነትም ያሳየናል።
በአስር መስመር ግጥም በተዋቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር (የዜግነት ክብር)ከመጀመሪያው ስንኝ ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ተዳስሰውበታል። ግጥሙ እንደ ቃል የተዘረዘሩትና እንደ መልዕክት የታመቁት እኩልነት፣ ፍትህ፣ ያልተሻረ ሰብዕና፣ አንድነት፣ ባህል፣ ሥራና ጀግንነት የዜጎች ክብር መሰረት መሆናቸውን ያስገነዝበናል።
ቃላቶቹ የደመቀ ትርጓሜና ግልፅነት የሚኖራቸው አሁን ካለው ሥርዓትና ካለፉት ጊዜ እውነታዎች ጋር እያነፃፀርን ስናያቸው ነው። ለምሳሌ አንድነት ስንል ምን ዓይነት አንድነት ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። ለምን ቢባል በደርግ ዘመን በነበረው «ኢትዮጵያ ቅደሚ…» ብሔራዊ መዝሙር ግጥም ውስጥ «አንድነት» ነበርና፤ «ለኢትዮጵያ አንድነት ለነፃነት…» የሚለው ማለት ነው።
ስለዚህም ከርዕዮተ ዓለም አንፃር የአሁኑን መዝሙር ግጥም ስንመለከት ግጥሙ ስለ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እየነገረን መሆኑን እንረዳለን። ዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚለው ገለፃ አሁን ካለው ርዕዮተ ዓለም ጋር በቀጥታ የተዛመደ ነው።
በዚህኛው የአሁን ዘመን የመዝሙር ግጥም ጎልተው የሚታዩን ሌላው የርዕዮተ ዓለም መገለጫዎች «ያልተሻረ ሰብዕና፣ ባህልና ፍትህ» ተብለው የተቀመጡት ቃላቶች ናቸው። እነዚህን ቃላቶችና ሃሳቦች ባለፉት መዝሙር ግጥሞች ላይ አናገኛቸውም፤ ቃላቶቹን አሁን ምን አመጣቸው ካልን ርዕዮተ ዓለም ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው መልሱ።
«ያልተሻረ ሰብዕና» የሚለው ገለፃ ከዚህ ቀደም የተጨቆነ ሰብዕና መኖሩን ያስገነዝበናል። የባህሉም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው። አውዱን ስንመለከት የምናገኘው መነሻ ከዚህ ቀደም በነበሩ ሥርዓቶች ህዝቦች ባህላቸውን፣ የባህላቸው መገለጫ የሆነ ቋንቋቸውንና ማንነታቸውን አጥተው ከርመዋል የሚል መልዕክት ይከሰትብናል። ፍትህ አልነበረም የሚለውን መልዕክትም ያሳየናል።
ከሀገራችን የዘርፉ ምሁራን እንደ ብርሃኑ ገበየሁ ያሉት «የሥነ ግጥማዊ ትንታኔ መዳኛውየተፃፈውን ቃል በራሱ የንባብ አውድና ባህሉ ባፀደቃቸው ኪናዊ ስምሪቶች ማንፀሪያነት መተርጎም ነው» ይሉናል።
ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያዊውን ባህልና አውድ ተመርኩዘን ግጥሙን እንደ ሌላው ሥነ ጽሑፍ ጊዜና ቦታ ከሚፈልገው ርዕዮተ ዓለም አንፃር ስንቃኘው የኢትዮጵያ ህዝቦችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማንነት የሚያቀነቅን ሆኖ እናገኘዋለን። ልዕለ ሃሳቡ ገንኖና የብዙዎች ሆኖ እንዲሄድ የሚያደርግ ጥልቅ አስተሳሰብ መኖሩንም እንረዳለን። ያለፈው ጊዜ መለወጡንም እናረጋግጣለን።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ትንታኔውን ሊያጠናክር የሚችል ሃሳብ ጎልቶ ይታይበታል። በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 4 «የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር» በሚለው ርዕስ ስር « የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ህዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በህግ ይወሰናል» ይላል።
ይህም ግጥሙ ገና ከመዘጋጀቱ በፊት ርዕዮተ ዓለማዊ አቅጣጫ ነበረው ማለት ይቻላል፤ የማህበረሰቡን ባህል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ቀድሞ ግምት ውስጥ አስገብቷል። የአሁኑን እምነታቸውንና የወደፊት ዕድላቸውንም ተልሟል።
በግጥሙ የርዕዮተ ዓለም አንዱ ፋይዳና ዋነኛ መገለጫ ይኸው መሆኑ እርግጥ ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ግጥም ከርዕዮተ ዓለም አንፃር የማርክስ ያልሆነ፣ የሌሎች ሶሻሊስታዊ ንድፈ ሃሳቦችንም የማያቀነቅን የኢትዮጵያውያን ህዝቦች ብቻ የርዕዮተ ዓለም ማቀንቀኛ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ስናከብርም በዚህ እውነትና ታሪክ መካከል በመሆናችን ለሀገራችን፣ ለሉዓላዊ ነታችን፣ በውስጣችን ላለው ልዩ ኢትዮጵያዊነት ልዩ ክብር ሰጥተን በማንነታችን ላይ የተነሱ የእኛዎቹን ቅኝ ገዢዎች እባካችሁ ታሪካችሁን እወቁ እያልናቸው ይሁን።