የኢትዮጵያን የአየር ክልል ያለፈቃድ ጥሰው የገቡ አምስት የሱዳን ሔሊኮፕተሮችና 26 አብራሪዎቻቸው ታስረው ተለቀቁ፡፡
ሩሲያ ሠራሽ የሆኑት አምስት የትራንስፖርት ሔሊኮፕተሮች
ንብረትነታቸው ተቀማጭነቱ ሱዳን ካርቱም የሆነ ሔሊኮፕተር አከራይ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው በሱዳን ሲቪል አቪዬሽን
ባለሥልጣን የተመዘገበ ሆኖ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የበረራ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አብራሪዎቹ ግን ምሥራቅ
አውሮፓውያን ናቸው ተብሏል፡፡ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከሦስት ሳምንት በፊት አምስቱ ሔሊኮፕተሮች የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ሳያስፈቅዱ ከካርቱም ወደ ባህር ዳር ጉዞ ይጀምራሉ፡፡ ሔሊኮፕተሮቹን የተከራየው የታንዛኒያ መንግሥት ሲሆን፣ አብራሪዎቹ ዓላማቸው ከካርቱም በኢትዮጵያን አድርገው፣ ኬንያ በመቀጠል ወደ ታንዛኒያ ማቅናት ነበር፡፡ ባህር ዳር አርፈው ነዳጅ ቀድተው ጉዟቸውን ለመቀጠል አቅደውም ነበር፡፡
ይህን ሁሉ ሲያቅዱ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የበረራ ፈቃድ (የኢትዮጵያን የአየር ክልል ለማቋረጥ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ለማረፍ) የሚሰጠውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንን አላነጋገሩም፡፡ ጉዳያችሁን አስጨርሳለሁ ያላቸውን አንድ የባህር ዳር ነዋሪ በሰጣቸው የመተማመኛ ቃል ብቻ ይዘው፣ የኢትዮጵያን የአየር ክልል በአማራ ክልል በኩል ጥሰው ገብተዋል፡፡
ጉዳዩን በከፍተኛ ንቃት ሲከታተል የነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰሜን ዕዝ የአየር መቃወሚያ ክፍል፣ ሔሊኮፕተሮቹን ዒላማ ውስጥ አስገብቶ ሲቃኛቸው እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ባለሙያዎችም በአገር አቀፍ ራዳር ሲከታተሏቸው እንደነበር ታውቋል፡፡
አምስቱም ሔሊኮፕተሮች በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሠረት ባህር ዳር ግንቦት 20 ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በሰላም አርፈዋል፡፡ ‹‹ሔሊኮፕተሮቹ የሲቪል እንደሆኑ በመታወቁ በተዋጊ ጄቶች ማጀብ አላስፈለገም፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡
ባህር ዳር እንዳረፉ ከሔሊኮፕተሮቻቸው በቀጥታ ወደ መኪና ገብተው በኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይሎች ታጅበው ወደ ማረፊያ ቤት መወሰዳቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ባለሙያዎች በአብራሪዎቹ ላይ ምርመራ ማካሄዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አብራሪዎቹ ያለፈቃድ የአንድ ሉዓላዊ አገር የአየር ክልል አልፈው በመግባታቸው የአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር በሚገኘው የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡
በተካሄደው ምርመራ አብራሪዎቹ ሌላ ተልዕኮ ኖሯቸው ሳይሆን በተሳሳተ አካሄድ ባህር ዳር አርፈው ነዳጅ ሞልተው ጉዟቸውን ወደ ታንዛኒያ ለመቀጠል በማቀድ ነው የሚል መተማመኛ ላይ በመደረሱ፣ ባለፈው ሳምንት አምስቱ ሔሊኮፕተሮችና 26 አብራሪዎች ተለቀው ከአገር መውጣታቸውን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
አብራሪዎቹ የተለቀቁት በዋስትና ሲሆን በቀጠሮአቸው ቀን ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኙ የሱዳን ዲፕሎማቶች አብራሪዎቹን ለማስለቀቅ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጉዳዩ በፍርድ ቤት የተያዘ ቢሆንም፣ በዲፕሎማሲያዊ ውይይት መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል ምንጮች ያላቸውን ግምት ገልጸዋል፡፡
ባህር ዳር አርፋችሁ ነዳጅ እንድትቀዱ ተፈቅዶላችኋል ብሎ ያሳሳታቸው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሔሊኮፕተሮች ነዳጅ የመያዝ አቅማቸው ውስን በመሆኑ ረዥም በረራ በሚያደርጉበት ወቅት በየቦታው በማረፍ ነዳጅ ይቀዳሉ፡፡ አንድ ሔሊኮፕተር በአማካይ በሰዓት 800 ሊትር ነዳጅ እንደሚጠቀም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ስለጉዳዩ የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል፡፡ የሱዳን ኤምባሲን በስልክ ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በ1992 ዓ.ም. ያለፈቃድ ወደ ኢትዮጵያ የአየር ክልል የገባ ዕቃ ጫኝ አውሮፕላን በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አየር መከላከያ ምድብ በተተኮሰ ቮልጋ ሚሳይል ተመትቶ መጋየቱን ያስታወሱት ምንጮች፤ ‹‹የኢትዮጵያ አየር ክልል እንዲያው ዝም ብሎ ዘው ተብሎ የሚገባበት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
በዚያን ወቅት አውሮፕላኑን ያበሩ የነበሩ ሁለት የስዊድን ዜግነት ያላቸው ፓይለቶች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ አውሮፕላኑ ከአሜሪካ በኪራይ የመጣ ሲሆን ወደ ሞዛምቢክ እየተጓዘ ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከማቅናቱ በፊት አስመራ አርፎ ነዳጅ ቀድቶ ነበር፡፡
፡- ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment