Monday, September 21, 2015

ታሪክን የኋሊት

መስከረም 06፣2008
የጀርመን ናዚዎች፣ ዓለምን የመቆጣጠር ክፉ ኃሳብ ባደረባቸው ጊዜ፣ ክፉ ኃሳባቸውን ፖላንድን በመውረር አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ አገሪቱን፣ በ20 ቀናት ሙሉ ለሙሉ፣ በመዳፋቸው አስገቧት፡፡ ፓላንዳውያን ፣አገራቸውን ከናዚዎች ወረራ ለመከላከል፣ የተቻላቸውን አደረጉ፡፡ የናዚዎች ዘመቻ፣ 16ኛ ቀኑን ባስቆጠረ ማግስት፣ ከምስራቅ አቅጣጫ፣ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ቀይ ጦር ወረራ መክፈቱ፣ ለፖላንዳውያኑ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነባቸው፡፡ ይህ ከሆነ፣ ዛሬ ልክ 76 ኛ ዓመቱን ደፈነ፡፡ ጀርመኖቹ ወረራ በጀመሩ በ20 ቀናቸው፤ ሶቪየቶቹ በ4 ቀናት ውጊያ ፖላንድን ተቃረጧት፡፡ ሶቪየት ህብረት፣ የፖላንድን ምስራቃዊ ግዛት የያዝኩት፣ የዩክሬንና የቤሎሩሲያን ግዛቶቼን ደህንነት ለማስጠበቅ ነው፣ የሚል ምክንያት አቀረበች፡፡
እውነታው ግን፣ ፖላንድ፣ በጀርመን ናዚዎች ልትወረር አንድ ሳምንት ሲቀራት፣ በጀርመንና በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ በተፈራረሙት፣ ሚስጥራዊ ስምምነት መነሻ ነበር፡፡ ሚስጥራዊው ስምምነት፣ የዚያን ጊዜዎቹን የሁለቱን አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስም በመያዝ፣ በታሪክ የሪቨንትሮፕ ሞሎቶቭ ስምምነት ተብሎ ይታወቃል፡፡ ስምምነቱ፣ ላይ ላዩን ያለመጠቃቃት ውለታ ቢመስልም፣ ሚስጥራዊ ክፍሉ የግዛት መሸንሰንና የተፅዕኖ ክልልን መፍጠርን የተመለከተ ነው፡፡ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት፣ የፖላንድን ምስራቃዊ ግዛት የያዘችውና ሦስቱን የባልቲክ አገሮች ኢስቶኒያ፣ላቲቪያና ሊትዌንያን ወደ ራሷ የቀላቀለችው፣ በዚሁ ሚስጥራዊ ስምምነት መነሻ ነው ይባላል፡፡ የሶቪየት ህብረትና የናዚዎቹ ያለ መጠቃቃት ውለታም ሆነ፣ ሚስጥራዊው ስምምነት፣ ብዙ ርቀት አልተጓዘም፡፡ የጀርመን ናዚዎች፣ ስምምነቱን ሶቪየት ህብረትን ለማዘናጋት ተጠቅመውበታል፡፡ ናዚዎቹ አቅማቸው መፈርጠሙ በተሰማቸው ጊዜ፣ ከሞስኮ ጋር የገቡትን ያለመጠቃቃት ውለታ አሸቀንጥረው ጣሉት፡፡ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ፣ ናዚ ጀርመን ሶቪየት ህብረትን ወረረች፡፡ ወረራው የቀድሞዋን ሶቪየት ህብረት በጦርነቱ ከተሳተፉ አገሮች ሁሉ፣ የላቀውን ዋጋ አስከፈላት፡፡ የ2ኛው የዓለም ጦርነት፣ ዋነኛዋ ቀንበር ተሸካሚ ሆነች፡፡ ሌላ ሌላው፣ ጥፋትና ውድመት፣ ወደ ጐን ቢባል እንኳ ፣ከ20 ሚሊዮን በላይ ዜጐቿን ሕይወት አስገብሯታል፡፡

ምንጭ:shegerfm.com

No comments:

Post a Comment