Monday, September 21, 2015

እኛና ስልካችን


ሰሚት አካባቢ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ ጊዜው ሕፃን አዋቂ ሳይባል በርካታ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በሚጾሙት ፍልሰታ ጾም ወቅት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያኑ መቅደስ የተገኙት ምእመናን የቅዳሴ መጀመርን ይጠባበቃሉ፡፡
አንዳንዶቹ በፀጥታና በዝምታ ተቀምጠዋል፡፡ ፀሎት የሚያደርጉም አሉ፡፡ በሠላሳዎቹ መጨረሻ እንደምትሆን የገመቷት ወጣት ሁኔታ እንዳስገረማቸው አጠገቧ የነበሩት እናት ይናገራሉ፡፡ ወጣቷ ቤተ መቅደስ ገብታ ከተቀመጠች ጀምሮ እጇና ዓይኗ ከስልኳ አልተለዩም፡፡ አንዴም ቀና ሳትል በዚህ ሁኔታ ረዥም ደቂቃዎችን አሳለፈች፡፡ ቅዳሴ ተጀመረ ተጋመሰም፡፡ ወጣቷ ቅዳሴ ሲጀመር ያስቀመጠችውን ሞባይል ስልኳን አንስታ ከፍ አድርጋ በመያዝ ፀሎት እንደሚያደርግ ሰው ሁሉ አሁንም አሁንም ትሰግዳለች፡፡ ልጅቷን በመገረም ሲከታተሉ የነበሩት እናት ወዲያው በስልኳ የፀሎት መጽሐፍ እያነበበች እንደሆነ ተረዱ፡፡
ታክሲ ላይ፣ ካፍቴሪያ፣ በስበሰባ አዳራሽ ሌላም ሌላም ቦታ ላይ አንድ ጠረጴዛ ተጋርተው ተጠጋግተው የተቀመጡ ጓደኛሞች እንኳ እርስ በርስ ከመጫወት ይልቅ ስልካቸውን መርጠው በስልክ ሲጠመዱ መመልከት የተለመደ እየሆነ ነው፡፡ ሁኔታው ሰዎች ከመቼውም በላይ ስልካቸውን የመረጡበት ጊዜ ነው ለማለት የሚያስደፍር ብዙ ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ፣ ለማስተዛዘን ከለቅሶ ቤት ተገኝተው፣ የቤተሰብ እራት ላይ፣ ስብሰባ ላይ ወይም ክፍል ውስጥ ሰዎች መልዕክት በመላክ ወይም በመመለስ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን በመመልከት፣ ፎቶ በማንሳት አልያም በመነሳት መጠመድ በብዛት እየተስተዋለ ያለ ትዕይንት ነው፡፡ ጥቂት የማይባሉ ስልካቸው ድምፅ አሰማም አላሰማም የትም ይሁኑ የት አሁንም አሁንም ስልካቸውን እያወጡ መመልከት ልምድ የሆነባቸው ይመስላል፡፡ ምንም ነገር እንዳያመልጠኝ በሚል ጥንቃቄ ወይም አንዳንድ ነገሮች፣ ኦን ላይን ያሉ ወዳጆች ቢያመልጡኝስ በሚል ሥጋት በማንኛውም ሰዓት የስልካቸውን ኢንተርኔት ኦን አድርገው የሚንቀሳቀሱም አጋጥመውናል፡፡
በሠላሳዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ወጣት ነው፡፡ በአንድ የግል ተቋም ውስጥ ኤክስፐርት ነው፡፡ ሁልጊዜም ስልኩ ኦን መሆኑን በተደጋጋሚም ስልኩን እንደሚመለከት ይናገራል፡፡ በተለይም ኢንተርኔቱን ክፍት የሚያደርገው ማኅበራዊ ድረ ገፆች ላይ የሚወጡ ነገሮች እንዲያመልጡት ስለማይፈልግ፤ ኦንላየን ከሚያገኛቸው ጓደኞቹ ጋርም ማውራት (ቻት ማድረግ) ስለሚፈልግ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
‹‹ከጓደኞቼ ጋር ምሳ ልበላ ቁጭ ብዬ ስልኬን ዓየት ላደርግ እችላለሁ ግን ሳልቆይ ቶሎ አስቀምጣለሁኝ፡፡ ቤትም ሌላ ቦታም ስልኬን አየት አደርጋለሁኝ ግን ብዙ አልቆይም›› ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው በቀን የሀምሳ ወይም የመቶ ብር ካርድ የሚጨርስ ቢሆንም ይህን እንደ ችግር አይቆጥረውም፡፡ ምክንያቱም ከጓደኞቹ ጋር ቻት ማድረጉንና ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ የሚወጡ ነገሮችን መከታተሉን እንደ ትልቅ ነገር ይመለከተዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም የብዙዎችን ስማርት ፎን መያዝ ተከትሎ ሰዎች ሁሉ ነገራቸው ከስልካቸው ጋር እየሆነ መሆኑን መታዘባቸውን ይናገራሉ አቶ ጌትነት አማረ፡፡ በአንድ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የትምህር ጥናትና ምርምር ኤክስፐርት ናቸው፡፡ ‹‹ሻይ ቡና ለማለት ከጓደኛው ጋር ቁጭ ብሎ አጠገቡ ያለውን ጓደኛውን ትቶ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ካለ ጓደኛው ጋር ቻት የሚያደርግ ብዙ ሰው አለ፡፡›› የሚሉት አቶ ጌትነት፣ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ አብሮ ያለው ሰው እንዴት ስልኩ ላይ ከተጠመደው ሰው ጋር ሊያወራ ሊጫወትስ ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የራሳቸውን ቤተሰብ ጨምሮ በቤት ውስጥ፣ ቢሮና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ዕለት በዕለት እየታየ እንዳለ በመግለጽ የባሰ ያሉትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ፡፡
ስብሰባ ላይ ነው፡፡ ጥናቷን በፕሮጀክተር በማቅረብ ላይ ያለችው ባለሙያ ጥያቄ ወይም አስተያየት ካለ ጠይቃ አሁንም አሁንም ስልኳ ወዳለበት ጥግ ሔደት እያለች ስልኳን ትመለከታለች፡፡ አንዴ ሁለቴ እንጂ አትደጋግመውም ብለው አሰቡ ታዳሚዎቹ፡፡ አቅራቢዋ ግን መለስ መለስ እያለች ስልኳን መነካካቷን ቀጠለች፡፡ ነገሩ የገረማቸው የሻይ ዕረፍት ላይ ለምን እንደዚያ እንደምታደርግ ጠየቋት፡፡ ከጠየቋት መካከል እሳቸው አንዱ ነበሩ፡፡
የአቅራቢዋ መልስ ‹‹ስልኬን በተደጋጋሚ መመልከቴ እኔን ምንም አይረብሸኝም እናንተም የምትሰጡትን አስተያየት በደንብ ነው የምከታተለው›› የሚል ነበር፡፡ እሷ ብቻ ሳትሆን ከሰው መካከል ሆነው በስልካቸው የሚጠመዱ በአካል በተገኙበት ቦታ የሚካሔደውን ነገር ከልብ አትከታተሉም ሲባሉ እንከታተላለን መሳተፍም እንችላለን ብለው እንደሚከራከሩ ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁለትና ከዚያ በላይ ነገሮችን ለማድረግ መሞከር አስቸጋሪ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው፡፡
‹‹ሰው ትልቅ ጉዳይ ለማዋየት ቀጥራቸው እንኳ አሁንም አሁንም ስልካቸውን ከመመልከት የማይቦዝኑ አሉ፡፡ መነጋገር የሚያምረው ዓይን ዓይን እየተያዩ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ሰው እንዴት ማውራቱን ሊቀጥል ይችላል? እኔ ከእንደዚህ ዓይነት ሰው ጋር ለመቀጣጠርም ፍላጐት የለኝም›› ይላሉ፡፡
እንደ እሳቸው እምነት የዚህ ዓይነቱ የሰዎች በሞባይል ስልክ መጠመድ ቤተሰባዊ፣ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲሁም ጓደኝነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ትኩረት ሰጥተው ሊከውኑት የሚገባውን ነገር በአግባቡ እንዳይከውኑ ስለሚያደርግ ውጤታማነትን በጣም ይቀንሳል፡፡
ምንም እንኳ ዘወትር ሞባይል ስልክ ላይ የመጠመድ ነገር በታዳጊዎች ላይ የሚያይል ቢሆንም የተማሩና የተረጋጉ በሚሏቸው ጐልማሶች ላይ መታዘባቸውን በመጥቀስ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ከብዙ ነገሮች አንፃር ስልክ በስልክ አይጠመዱም የሚባሉ ሰዎች እንኳ ከስልካችን አንለይ ያሉበት ጊዜ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
‹‹ሁሌም ስልክ ላይ መሆን ዘመን የተሻገሩ የማኅበራዊ እሴቶችን ይሸረሽራል፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ሰዎች መቼ ነው ከስልክ ከኢንተርኔት ዓለም ውይይታቸው ራሳቸውን ገትተው በአካል በተገኙበት ቦታ ወዳሉ ሰዎች ትኩረታቸውን የሚመልሱት?›› ሲሉ በመጨረሻ ጥያቄአቸውን ይሠነዝራሉ፡፡
ትራፊክ ፖሊስ በማይኖርባቸው ቦታዎች ላይ ስልካቸውን እያዩ፣ መልዕክት እየመለሱና ስልክ እያነጋገሩ የሚያሽከረክሩ ጥቂት እንዳልሆኑ በአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ ሕዝ ግንኙነት ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ይገልጻሉ፡፡ አስረግጦ ለመናገር ጥናት የሚያስፈልግ ቢሆንም በተደጋጋሚ ከሚታዩ አጋጣሚዎች በመነሳት በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ በስልክ ምክንያት የሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ጥቂት እንደማይሆኑም ይገምታሉ፡፡
በዘንድሮው የፈረንጆች ዓመት አሜሪካ ውስጥ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው በጥናቱ ከተካተቱ 77 በመቶ የሚሆኑት መንገድ ላይ እየሔዱ በማንኛውም መንገድ ስልካቸውን መጠቀም ችግር የለውም ብለው የሚያስቡ ሲሆን፣ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት መደብር ውስጥ ተሰልፈው ወይም በሕዝብ መተላለፊያዎች ስልካቸውን መጠቀማቸው ችግር እንደሌለው ያምናሉ፡፡ ከ88 በመቶ በላይ የሚሆኑት ቤተሰብ ተሰብስቦ እራት እየበላ፣ ስብሰባ ላይ፣ በፊልም ወይም በቴአትር አዳራሽ እንዲሁም በአምልኮ ቦታ ስልክ መጠቀም ተገቢ አይደለም ብለው የሚያምኑ ቢሆንም ተግባራቸው ግን በተቃራኒው መሆኑን ጥናቱ ያሳያል፡፡
የሰዎች ሁልጊዜም ስማርት ፎናቸውን ኦን ማድረግና ስልካቸውን ሳይመለከቱ ደቂቃዎች እንዲያልፉ አለመፈለግ ከፍተኛ ችግር እየሆነ መሆኑን ጥናቱ ይደመድማል፡፡ የመደምደሚያው መሠረት የሰዎች በእውነተኛው ዓለም ከጐናቸው ከተቀመጠ ሰው ይልቅ ትኩረታቸው በስልክ ሲያዝና ፍላጐታቸው በአካል አብሯቸው ካልሆነ ሰው ጋር መነጋገር መሆን መሠረታዊ የሰው ልጆችን የግንኙነት ዘዬ ይረብሻል የሚል ነው፡፡ በጥናቱ የተጠቀሰው ሌላው ችግር ደግሞ አጠገብ ካለ ሰው ይልቅ በስልክ የመጠመድ ነገር በፊት በፊት ይተች የነበረ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ተቀባይነት እያገኘና እንደ መደበኛ ነገር እየተቆጠረ ብዙዎችም እዚህ መስመር ውስጥ እየገቡ መሆኑ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሺዮሎጂ ዲፓርትመንት መምህር የሆኑት ተባባሪ ፕሮፌሰር ኢዛና ዐምደወርቅ በሞባይል ስልክ የመጠመድ ነገር በስፋት እየታየ መሆኑን ይህም በራሳቸው ዋጋ ያላቸውን ማኅበራዊ ግንኙነቶችን እየረበሸ ሰዎችን ወደ አርቴፊሻል ግንኙነቶች እያሻገረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ቀን በትምህርትና በሥራ ተወጥረው የማይገናኙና የማይተያዩ የአንድ ቤተሰብ አባላት ምሽት ላይ ለግማሽ ወይም ለአንድ ሰዓት ራት ላይ ሲገናኙ እንኳ ስልካቸውን ለመተው አለመፈለግ የችግሩን ስፋት እንደሚያሳይ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ተለምነው እራት የሚበሉም አሉ፡፡ በሕይወታቸው ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ካላቸው ቤተሰቦቻቸው ይልቅ ከማያይዋቸው ሩቅ ካሉ ምናልባትም እየቆዩና በመሀል እየጠፉም ከሚመልሱላቸው ጓደኞቻቸው ጋር ቻት ማድረግን የሚመርጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ የኢንተርኔት ግንኙነት በብዙ መልኩ እውነተኛውን ግንኙነት አይስተካከለውም አርቴፊሻል ነው፡፡›› ይላሉ፡፡
በስልክ መጠመድ እንደ አዲስ አበባ ባሉና በሌሎች ትልልቅ ከተማዎች ብቻም ሳይሆን በትንንሽ ከተሞችም ቦታ ሳይመረጥ መማሪያ ክፍል፣ ለቅሶ ቤት፣ ሠርግ ላይ እንዲሁም ትልልቅ አገራዊ ስብሰባዎች ላይም እየተስተዋለ መሆኑን መታዘባቸውን ይናገራሉ ተባባሪ ፕሮፌሰሩ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ስብሰባዎች ላይ ወይም ክፍል ውስጥ ሆኖ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ማየት ወይም የስልክ መልዕክት ማንበብም ሆነ መመለስ እንደተለመደ ነገር እየታየ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ምሥራቅ አፍሪካ ላይ ስማርት ፎን ይዞ መታየት የሚያኮራ ነገር ሆኖ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ በተለይም ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው ስማርት ፎኖች ገበያውን በማጥለቅለቃቸው ሊቀየር ችሏል፡፡ እንደ ህዋዌ፣ ቴክኖና ዜድቲኢ ያሉ የቻይና ኩባንያዎች በዚህ ሒደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተጠቃሚዎች የሚሆኑ ስልኮችን የሚያቀርበው ሳምሰንግም በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው፡፡
እየጨመረ ያለውን የሰዎችን በስማርት ፎን መጠመድ በመመልከት የተለያዩ አገሮች ለችግሩ ምላሽ እየሰጡ ነው፡፡ በኢንተርኔትና እንደ ሞባይል ባሉ ዲጂታል ቁሶች መጠመድ እንደማንኛውም ሌላ ሱስ እንዲታይ ማድረግ የመጀመሪያው ዕርምጃ ሲሆን፣ ከዚህ ሱስ ማገገቢያ ማዕከል እስከማዘጋጀት የገፉም አሉ፡፡ ለምሳሌ በሴንጋፖር በስልክ ሱስ ለተያዙ የምክር አገልግሎት ማዕከሎች አሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ የኢንተርኔትና የሞባይል ስልክ ሱስ እንደ አእምሯዊ ጤና መዛባት መታየት አለበት የሚል ክርክር የሚያነሱ የሥነ አእምሮ ሐኪሞችም አሉ፡፡
ቀደም ሲል ከስማርት ፎኖች ጋር በተያያዘ ጐልቶ ይታይ የነበረው ችግር በሞባይል ጌሞች መጠመድ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የማኅበራዊ ድረ ገጾች ሱስ እያየለ መምጣቱን መረጃዎች ያመለክታሉ::
ምንጭ:http://ethiopianreporter.com

No comments:

Post a Comment