Tuesday, October 14, 2014

የኢራፓ ም/ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ፓርቲውን ለቀቁ

በፕሬዚዳንቱ አምባገነንነትና ኢሕአዴግ በሰጠው ገንዘብ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል
- ‹‹አመራሮቹ የተናገሩት ሁሉ ሐሰት ነው›› የፓርቲው ፕሬዚዳንት
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ፣ አምስት የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት አመራሮች ከፓርቲው ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታወቁ፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ተሾመ ወልደ ኃዋርያት፣ አቶ ደረጀ ግርማ፣ ወ/ሪት መስታወት ስመኝ፣ አቶ ማሙሸት መኮንንና አቶ ኤርሚያስ ኤርሴሎ ከፓርቲው ራሳቸውን ለማግለል የተገደዱት የፓርቲው ፕሬዚዳንት አምባገነን በመሆናቸው፣ በትክክል የፓርቲውን ሥራ ሊሠሩ ባለመቻላቸውና ኢሕአዴግ ለፓርቲው ሥራ ማስፈጸሚያ የሰጠውን ገንዘብ ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር ለፓርቲው አበድሬያለሁ›› በማለት ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት በማሳወቃቸው ምክንያት መሆኑን፣ አመራሮቹ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡  Ethiopia Raeie Party logo
የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ለፓርቲው ሥራ አመራር ያስተላለፈውን አደራና የፖለቲካ ኃላፊነት ፕሬዚዳንቱ በኅብረት እንዲመራ ከማድረግ ይልቅ መሰናክል መሆናቸውን የሚናገሩት አመራሮቹ፣ ፕሬዚዳንቱ እየፈጸሙ ያሉትን ሕገወጥ ተግባር በማጋለጥ ራሳቸውን ከፓርቲው ማግለልን እንደ አማራጭ መውሰዳቸውን በመግለጫቸው አካተዋል፡፡ 
አንድ ፓርቲ በመሠረታዊነት የአባላቱን ጥቅምና ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅና በሕዝብ የሚሰጠውን ሥልጣን ተግባራዊ ለማድረግ ሕጋዊ መነሻ ይዞ መታገል ቢሆንም፣ የኢራፓ ፕሬዚዳንት ለሕዝብ ጥቅም ከመቆም ይልቅ፣ ግለሰባዊ ጥቅም በማስጠበቅ ሥራ ላይ መሰማራታቸው ስላሠጋቸው የለፉለትን ፓርቲ ለመልቀቅ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ 
አምባገነናዊ የጠቅላይነት አሠራርን መከተል የሚያስከትለውን አደጋ ከወዲሁ መገመት መቻላቸውን የሚናገሩት ከፍተኛ አመራሮቹ፣ መሠረት ያስያዙትንና የለፉለትን ፓርቲ ጥለው ሊወጡ መገደዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና ሁለት ጸሐፊዎች በፕሬዚዳንቱ አምባገነናዊ አመራር ተማረው መልቀቃቸውንም አስታውቀዋል፡፡ 
‹‹ራዕይ ከላይ ተሰጥቶኛል፣ ከሰማይ ወርዶልኛል፣ ኢትዮጵያን ትመራለህ ብሎ መንፈስ ስለነገረኝ ከአሜሪካ መጥቻለሁ…›› በማለት የኢራፓ ፕሬዚዳንት እንደሚናገሩ የሚገልጹት አመራሮቹ የምድሩንና የሰማዩን በመደበላለቅ፣ ፓርቲውን ለከፋ ጉዳት እየዳረጉት መሆኑን የፓርቲው አባላት እንዲያውቁት ማድረጋቸውንም አመራሮቹ በመግለጫው አስረድተዋል፡፡ 
አመራሮቹ እንደገለጹት ኢራፓ በፖለቲካ ፓርቲዎች አገር አቀፍ የጋራ ምክር ቤት አባልነቱ፣ ለፓርቲው ፖለቲካዊ ሥራዎችና እንቅስቃሴዎች ብቻ እንዲውል ኢሕአዴግ 191,898 ብር ከ35 ሣንቲም የሰጠው ቢሆንም፣ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ራሳቸው አበዳሪና ተበዳሪ ሆነው ‹‹አንድ ሚሊዮን ብር አበድሬያለሁ›› በማለት 78,898 ብር ለግላቸው መውሰዳቸውንና ይህ ደግሞ ሕገወጥ መሆኑን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡ 
በሰሜን አሜሪካና በሌሎች ቦታዎችም በፓርቲው ስም የሚሰበሰብ የዕርዳታ ገንዘብ ለግል ጥቅም እየዋለ መሆኑን የሚጠቁሙት አመራሮቹ፣ በአጠቃላይ ፓርቲው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፖለቲካን ለመምራት በማያስችልና በማይመጥን አደረጃጀት፣ ዕውቀትና ክህሎት በሌለው አመራር እየተመራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የፓርቲን ስም፣ ማሕተምና ሠርተፊኬት ስለተያዘ ብቻ የፓርቲውን አሠራር አንድ ግለሰብ አጠቃሎ ሊይዝ ስለማይገባ በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመሥርተው፣ እውነተኛ ፖለቲካ ከሚያራምዱ ፓርቲዎች ጋር ለመሥራት በመወሰን ከኢራፓ ራሳቸውን ማግለላቸውን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም እንዲገነዘበው ማሳሰባቸውን አስታውቀዋል፡፡
ራሳቸውን ከፓርቲው እንዳገለሉ በመግለጽ የሆነ ያልሆነውን በመናገር የእሳቸውን ስም ሆን ብለው ከማጥፋት የዘለለ እውነታ እንደሌለውና አመራሮቹ የሚሉት ሁሉ ሐሰት መሆኑን በማስረጃ እንደሚያረጋግጡ፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተሾመ ወልደ ኃዋርያት በፈጸሙት የዲስፒሊን ግድፈት ምክንያት መታገዳቸውን የገለጹት አቶ ተሻለ፣ ከአቶ ኤርሚያስና አቶ ተስፋዬ በስተቀር ሌሎቹ ከፓርቲው ጋር መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ አቶ ተሾመ ከሥራ አመራሩ ዕውቅና ውጪ ለሪፖርተር መግለጫ በመስጠታቸው እንዲያብራሩ ሲጠሩ ባለመቅረባቸው፣ ከስምንት ሥራ አመራር ኮሚቴ ውስጥ በስድስቱ ሙሉ ድምፅ መታገዳቸውን ደግመው አስረድተዋል፡፡ 
ከኢሕአዴግ የተሰጠውን ገንዘብ በሚመለከት አቶ ተሾመ ስምንት ሺሕ ብር መውሰዳቸውን የገለጹት አቶ ተሻለ፣ እሳቸው ግን ላለፉት ስድስት ዓመታት አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለፓርቲው ማውጣታቸውን ከማሳወቅ ባለፈ፣ ምንም የወሰዱት ገንዘብ እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ የተሰጠው ገንዘብ ከቤት ኪራይ፣ ከሠራተኛ ደመወዝ፣ ከስብሰባና ከተለያዩ ወጪዎች የሚያልፍ ባለመሆኑ የተባለው ሁሉ ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማሙሸት የሚባሉት አባል አመራር አለመሆናቸውንም አክለዋል፡፡ ፓርቲን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር መቻል አምባገነን ሊያስብል እንደማይችልም አክለዋል፡፡ 
———

No comments:

Post a Comment