ላለፉት ዓመታት የቅጂና ተዛማች መብቶች ጥሰት በፈጠረው ስጋት ተቀዛቅዞ የከረመው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ዘንድሮ የተነቃቃ ይመስላል፡
ታዋቂ ድምፃውያን ለአዲሱ አመት አዳዲስ ነጠላ ዜማቸውንና አልበማቸውን አበርክተዋል፡፡ ይሄም ለሰሞኑ የአውዳመት ድባብ ተጨማሪ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ፣ የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”፣ የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው” የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”፣ የቤተልሔም ዳኛቸው “ሰው በአገሩ” እና የተስፋፅዮን ገ/መስቀል “ጀመረኒ” እንዲሁም የቴዎድሮ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማም ለአዲስ ዓመት ከተበረከቱ የሙዚቃ ስራዎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡
“ሙዚቃ እንደ በረዶ በቀዘቀዘበት ዘመን ደፍረውና መስዋዕትነት ከፍለው አዲስ ነገር ይዘው ስለመጡ አድናቆት ይገባቸዋል” ብለዋል በአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የስራ ኃላፊ የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፡፡
በዚህ አመት ለአድማጭ ይበቃሉ ከተባሉት የሙዚቃ አልበሞች መካከል፣ የኤፍሬም ታምሩ አልበም የሚጠቀስ ሊሆን፣ የድምፃዊው ወላጅ እናት በሳምንቱ መጀመሪያ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ምክንያት አልበሙ ሳይለቀቅ ቀርቷል፡
የአብነት አጎናፍር “አስታራቂ”
ከሁለት ሳምንት በፊት ገበያ ላይ የዋለው አብነት አጎናፍር “አስታራቂ” አልበም 14 ዘፈኖች የተካተቱበት ሲሆን ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሀይሉና አቤል ጳውሎስ አቀናብረውታል፡፡ ድምፃዊው ሶስተኛ ስራው በሆነው በዚህ አልበም አገራዊ፣ ማህበራዊ እና የፍቅር ጉዳዮችን የዳሰሳ ሲሆን ከአድማጮች በተገኘ አስተያየት፣ ከአብነት ስራዎች ውስጥ ስለአገር የዘፈናቸው “አያውቁንም”፣ “ለማን ብዬ”፣ “አስታራቂ” እና “የኔ ውዳሴ” የተሰኙት ይበልጥ ተወደዋል፡፡ በAB ሙዚቃና ፊልም ፕሮዳክሽን የታተመው “አስታራቂ” አልበም፤ በአርዲ ኢንተርቴይመንት እየተከፋፈለ ሲሆን የአዲሱ ዓመት አንዱ ገጸ በረከት ነው፡፡ አብነት ከአማርኛ ሙዚቃ በተጨማሪ ሱዳንኛ እንደሚጫወት የሚታወቅ ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ “አያሌሌ” የተሰኘ የጉራጊኛ ዘፈን አካትቷል፡፡ ድምፃዊው በአብዛኛው ዘፈኖቹ ላይ በግጥምና በዜማ ድርሰት ተሳትፏል፡፡
የታምራት ደስታ “ከዛ ሰፈር”
ለአዲሱ ዓመት በገፀ-በረከትነት ከቀረቡት አልበሞች ውስጥ የታምራት ደስታ አራተኛ ስራ የሆነው “ከዛ ሰፈር” አንዱ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ለአድማጭ ጆሮ የደረሰው ይሄው አልበም፤ 14 ዘፈኖችን አካትቷል፡፡ ካሙዙ ካሳ፣ ሚካኤል ሃይሉ፣ ሚካኤል መለሰና ኪሩቤል ተስፋዬ በቅንብር የተሳተፉበት ይሄ ስራ፤ በግጥም እና ዜማ ጌትሽ ማሞ አማኑኤል ይልማ፣ መሰለ ጌታሁንና ኢዩኤል ብርሃኔን አሳትፏል፡፡ በናሆም ሪከርድስ አሳታሚና አከፋፋይነት ገበያ ላይ የዋለው የታምራት አልበም፤ በስፋት እየተደመጠ ሲሆን በተለይም “ሊጀማምረኝ ነው” “አዲስ አበባ”፣ “ማማዬ” እና የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “ከዚያ ሰፈር” የተሰኙ ዘፈኖች የበለጠ እየተሰሙ እንደሚገኙ ከአድማጮች አስተያየት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ”
ከበደሌ ጋር አመቱን ሙሉ በሚዘልቅና “ወደ ፍቅር ጉዞ” በተሰኘ የሙዚቃ ኮንሰርት ከአድናቂዎቹ ጋር ለመገናኘት የጀመረው ስራ የተሰናከለበት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፤ ከሁለት ሳምንታት በፊት የለቀቀው “ሰባ ደረጃ” የተሰኘ ነጠላ ዜማው በስፋት እየተደመጠ ሲሆን ማህበራዊ ድረ - ገፆችን በተለይም ፌስ ቡክን ተቆጣሮጥት ሰንብቷል፡፡ የቴዲ “ሰባ ደረጃ” ፒያሳ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ሰራተኛ ሰፈር፣ አራት ኪሎን፣ ታሪካዊ ክስተቶችንና አለባበሶችን ከፍቅር ጋር እያሰናሰለ ያነሳሳል፡፡ የቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ” ነጠላ ዜማ ሙሉ አልበምን የመወከል ያህል ተቀባይነት አግኝቶ በየምሽት ቤቱ፣ በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ በስፋት እየተደመጠ ያለ የአዲስ አመት የበዓል ድምቀት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የሰለሞን ሃይለ “ውህብቶ”
“ቆሪብኪለኩ” (ቆረብኩልሽ) በሚለው የመጀመሪያ አልበሙ በተለይም “ንኢባባ” በተሰኘው ዘፈኑ የሚታወቀው ወጣቱ የትግርይኛ ዘፋኝ ሰለሞን ሃይለም ከሳምንታት በፊት “ውህበቶ” የተሰኘ አልበም ለአድማጭ አቅርቧል፡፡ አልበሙ 12 ዘፈኖችን ያካተተ ሲሆን፣ ስለ ሃገር፣ ስለ ፍቅር ስለማህበራዊ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ ሙሉ ግጥምና ዜማው በራሱ በድምፃዊው የተሰራ ሲሆን፣ በቅንብሩ አብዛኛውን ዘፈኖች ተወልደ ገ/መድህን ሲሰራ፣ ሁለት ዘፈኖችን ዮናስ መሃሪ እና ደነቀው ኪሮስ፣ አንዱን ዘፈን ዘመን አለምሰገድ አቀናብረውታል፡፡ በስፋት እየተደመጠም ይገኛል፡፡
የዮሴፍ ገብሬ “መቼ ነው”
ድምፃዊና ጋዜጠኛ ዮሴፍ ገብሬም አዲሱን አመት ምክንያት በማድረግ “መቼ ነው” የተሰኘ አዲስ የሙዚቃ አልበሙን ከ10 ቀናት በፊት በገበያ ላይ አውሏል፡፡ ለዝግጅት 6 አመታትን የፈጀው ይሄው አልበም፤ በአገር፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመተሳሰብ ላይ የሚያተኩር ሲሆን 7 አቀናባሪዎችና የተለያዩ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች ተሳትፈውበታል፡፡ “መቼ ነው” የተሰኘው የአልበሙ መጠሪያ፣ “ክፉ አይንካብኝ” ሲል ስለ አገር የዘፈነው፣ “ፍቅር ነው ያገናኘኝ” እንዲሁም ስለአንድነትና መተባበር (በጉራጊኛ) የዘፈናቸው ይበልጥ ተወዳጅ እንደሆኑለት ከአድማጮች ያገኘነው አስተያየት ይጠቁማል፡፡ አልበሙ በተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎች በስፋት እየተደመጠ ይገኛል፡፡
የቤተልሔም “ሰው በአገሩ”
በ1996 ዓ.ም ለአድማጭ ባቀረበችው “ቅዳሜ ገበያ” የተሰኘ ባህላዊ ዜማዋ የምትታወቀው ድምፃዊት ቤተልሔም ዳኛቸው፣ ሰሞኑን “ሰው በአገሩ” የተሰኘ አዲስ አልበሟን ለአድማጭ አቅርባለች፡፡
ነዋሪነቷ በስዊዘርላንድ የሆነው ድምፃዊት ቤተልሔም ያቀረበችው አዲስ አልበም፤ 13 ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ነው፡፡ ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪና የድምፃዊቷ ባለቤት ዳዊት ጥላሁን ባቀናበረው በዚህ አልበም ውስጥ ራሱ ዳዊትና ቤተልሔም ጥላሁን በዜማና ግጥም ደራሲነት ተሳትፈዋል፡፡
የተስፋፅዮን “ጀመረኒ”
በባህላዊ የማሲንቆ አጨዋወቱ አድናቆት የተቸረው ድምጻዊ ተስፋፅዮን ገ/መስቀል ከሰሞኑ “ጀመረኒ” የተሰኘውንና ራሱን በማሲንቆ ያጀበበትን የትግርኛ ሙዚቃዎች ለአድማጭ አብቅቷል፡፡ ከዚህ ቀደም “ቆልዑ ገዛና” የተሰኘ አልበም አውጥቶ ተቀባይነትን ያገኘው ድምፃዊው፤ በ“ጀመረኒ” አልበሙ የሰርግን ጨምሮ በበርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 13 ሙዚቃዎችን አካትቷል፡፡ አልበሙን ዳአማት መልቲ ሚዲያ አሳትሞ እያከፋፈለው ሲሆን፣ ለአዲሱ ዓመት በተለይ በትግርኛ ዘፈን አድማጮች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
“አራዳ” ቪሲዲ ኮሌክሽን
በመስፍን ታምሬ ፕሮዲዩሰርነት የታተመውና 14 እውቅ ድምፃዊያን የተሳተፉበት “አራዳ” ባህላዊ እና ዘመናዊ ዘፈኖች በምስል (በቪዲዮ) የቀረቡበት ነው፡፡ የዚህ ቪሲዲ አዘጋጅ “ኢቫንጋዲ ፕሮዳክሽን” ሲሆን “ፒያሳ ዘ አራዳ ኢንተርቴይመንት” አሳትሞ ከትናንት ጀምሮ እያከፋፈለው ይገኛል፡፡ በ“አራዳ” ኮሌክሽን ቪሲዲ ላይ ሸዋንዳኝ ሃይሉ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ እመቤት ነጋሱሲ (ሰንዳበል)፣ ጃኪ ጎሲ፣ የኦሮምኛ ዘፋኙ አበበ ከፍኔና ቤተልሄም ዳኛቸውን ጨምሮ 14 ያህል ታዋቂ ድምፃዊያን ተሳትፈውበታል፡፡
“አራዳ” ብቸኛው ለአዲስ ዓመት የተዘጋጀ ቪሲዲ እንደሆነ ታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment