ሁለት የቻይና ኩባንያዎች፣ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ
ግንባታ ፕሮጀክት ሊሰጣቸው ነው፡፡ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቱ በምዕራብ ኢትዮጵያ ከሸካ ተራሮች ተነስቶ ወደ ባሮ
በሚፈሰውና ገባ ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ላይ የሚካሄድ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ በዚህ ሳምንት ሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2006
ዓ.ም. የሚሰጣቸው ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች ኃይድሮ ቻይናና ቻይና ገዞባ ግሩፕ ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በተለይ
ኃይድሮ ቻይና በገናሌ፣ ዳዋ፣ ጨሞጋ ያዳና ለፊንጫ በአመርቲነሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ አፈጻጻማቸው
ደካማ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ኩባንያዎቹ እንዲያሻሽሉ በተለያዩ ጊዜያት ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ገዞባ ግሩፕ የገናሌ ዳዋ ቁጥር ሦስት ኃይል ማመንጫ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በ2007 በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ቢታቀድም፣ የኩባንያው የሥራ አፈጻጸም 56 በመቶ ብቻ በመሆኑ በሁለት ዓመት ይዘገያል ተብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ይህ ኩባንያ ፊንጫ አመርቲነሽ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክትን የገነባ ሲሆን፣ የማረሚያ ሥራዎችን እንዲያካሂድና ፕሮጀክቱን እንዲያስረክብ ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል፡፡ ነገር ግን እስካሁን ማረሚያዎቹን አከናውኖ ፕሮጀክቱን እንዳላስረከበ ታውቋል፡፡
ነገር ግን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ይህንን አይቀበሉትም፡፡ አቶ ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህ ኩባንያዎች ይህ ሥራ እንዳይሰጣቸው የሚያደርግ የአፈጻጸም ችግር የለባቸውም፡፡ ‹‹የገናሌ ዳዋ ፕሮጀክት ትልቅ ተራራ መናድን ይጠይቃል፡፡ አፈጻጸማቸውም 56 በመቶ ሳይሆን 60 በመቶ ነው፡፡ የአመርቲነሽም ቢሆን ሥራ እንዳይሰጥ የሚያደርግ አይደለም፤›› ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
በሌላ በኩልም ‹‹የጨሞጋ ያዳ ፕሮጀክት የኩባንያው ችግር አይደለም፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ዓለማየሁ፣ ፕሮጀክቱ መካሄድ ያልቻለው በፋይናንስ ችግር ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኩባንያዎቹ ብቁ አይደሉም የሚያስብል ደረጃ ላይ አይደሉም፤›› በማለት አቶ ዓለማየሁ በኩባንያዎቹ ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ኃይድሮ ቻይና ደግሞ ከሰባት ዓመት በፊት አማራ ክልል ደብረ ማርቆስ አካባቢ የጨሞጋ ግየዳ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ለመገንባት ውል ተፈራርሟል፡፡ ነገር ግን ፋይናንስ አልተለቀቀም በሚል ምክንያት ሥራውን እንዳልጀመረና ድርጅቱ ሥራውን መልክ እንዲያሲዝ ሲጠየቅ መሰንበቱን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ምንጮች እነዚህ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ሥራው ለእነዚህ ኩባንያዎች እንዴት ሊሰጥ ይችላል? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች በገባ ወንዝ ላይ የሚያካሂዱትን ፕሮጀክት የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ከሆኑት ሱር ኮንስትራክሽንና የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ጋር በእሽሙር ግንባር (ጆይንት ቬንቸር) እንዲያካሂዱ መወሰኑን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የገባ ወንዝ ከጂማ ከተማ፣ ወደ ሸካ ዞን ዋና ከተማ ማሻ በሚወስደው መንገድ የጨዋቃ ሻይ ልማት እርሻ ከመድረሱ በፊት የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ ወንዝ ላይ የሚካሄደው ግንባታ በአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲደረግ ማስገደዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት የተቀላቀሉት ሁለቱ የቻይና ኩባንያዎች፣ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከአገራቸው እንደሚያመጡ በመግለጽ ድርድር በማድረጋቸው የመንግሥትን ይሁንታ አግኝተዋል፡፡ አቶ ዓለማየሁ እንደገለጹት ስምምነቱ በዚህ ሳምንት ሰኞ ጳጉሜን 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ይፈረማል፡፡
ለዚህ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው ከቻይና ኤግዚም ባንክ ይገኛል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ ገንዘብ መገኘቱ እንደተረጋገጠ፣ አራቱ ኩባንያዎች ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ከወንዙ የሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል በሚቀጥለው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እንደሚካተት ተገልጿል፡፡
No comments:
Post a Comment