Monday, September 8, 2014

‹‹በኢትዮጵያ ያለው የነዳጅ ጥራት ችግር ነዳጅ ቆጣቢና ዘመናዊ መኪኖችን እንዳናቀርብ አድርጐናል››









ጄፍሪ ኒሜዝ፣ ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገሮች
የፎርድ ኩባንያ ፕሬዚዳንት
ለደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የፎርድ ሞተር ኩባንያ ፕሬዚዳንትና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ከአራት ዓመታት በፊት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮም ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገሮችም ይህንኑ ኃላፊነት ይዘው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡
ዋና ማምረቻ ፋብሪካዎቹን በደቡብ አፍሪካ ከተከለ 91 ዓመታትን ያስቆጠረው ፎርድ ኩባንያ፣ በታዋቂው ሔንሪ ፎርድ እ.ኤ.አ. በ1903 ነበር የተመሠረተው፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት አዲስ አበባ የተገኙት ጄፍሪ ኒሜዝ፣ በኢትዮጵያ ፎርድ ኩባንያ አቅርቦቱን ለማስፋፋት እንደሚፈልግ፣ እግረ መንገዱንም እንደ የውጭ ምንዛሪና በነዳጅ ጥራት ላይ ከመንግሥት ጋር ለመምከር መምጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፎርድ ሞተር፣ እ.ኤ.አ. እስከ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ ለመካከለኛው ምሥራቅና ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገሮች 25 አዳዲስ ምርቶችን ለማቅረብ ከማቀዱ ጋር በተያያዘ፣ በኢትዮጵያ የፎርድ ወኪል ከሆነው ሬስ ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ጋር ለመነጋጋር መምጣታቸውም ታውቋል፡፡ ሬስ ኢንጂነሪግ ከ80 በመቶ በላይ የገበያ ድርሻው የኮንስትራክሽን ማሽነሪ የሆኑትን የካተር ፒላር ኩባንያ ምርቶችን በማስመጣት፣ ለመንግሥትና ለግል ፕሮጀክቶች እያቀረበ የሚገኝ አንጋፋ ኩባንያ ነው፡፡ ከሁለቱ የአሜሪካ ኩባንያዎች በተጨማሪ የሜሲ ፈርጉሰን ኩባንያ ሥሪት የሆኑ የግብርና ማሽነሪዎችንና የሌሎች ኩባንያዎችን ማሽኖች፣ የኃይል አቅርቦት መቆጣጠሪያ መሣሪዎችንና ሌሎችንም ያስመጣል፡፡ ከሬስ ኢንጂነሪንግ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ጄፍሪ ኒሜዝ ከሪፖርተርና ከሌሎች ሚዲያዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል፡፡ ይህንን ቃለ ምልልስ ብርሃኑ ፈቃደ አጠናቅሮታል፡፡
ጥያቄ፡- ፎርድ ኩባንያ ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እ.ኤ.አ. እስከ 2020 ድረስ የ40 በመቶ የመኪና ሽያጭ ሊኖረው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ ተመልክቷል? ስለኢትዮጵያ የተሠሩ አኃዞች ካሉ ቢገለጹልን?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ የሆነ የዕድገት አቅም ላይ እንደምትገኝ እናምናለን፡፡ በቀጣናችን 67 ገበያዎች አሉን፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም እንዳላት እናምናለን፡፡ ጠንካራ መንግሥት አለ፡፡ የሕግ የበላይነት፣ ፈጣን ዕድገት ያለው ኢኮኖሚ፣ ጥሩ ሥርዓተ ትምህርት በመኖሩ ኢትዮጵያ ከአማካይ በላይ አቅም እንዳላት እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን አኃዞችን ነጣጥለን ለኢትዮጵያ ምን ያህል ነው ብለን አላወጣንም፡፡ የ40 በመቶው ዕድገት ለእያንዳንዱ የተናጠል ገበያም የተከፋፈለ አይደለም፡፡
ጥያቄ፡- እንደ ቶዮታ፣ ኒሳንና ኪያ የመሳሰሉ ተቀናቃኞችን እንዴት ትመከታላችሁ? እያንዳንዱ ሰው ሊገዛ በሚችለው አቅም መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ ወይም በምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ለማቅረብ አማራጭ ሐሳብ አላችሁ?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ በዓለም ላይ ፉክክር ከሚበዛባቸው ኢንዱስትሪዎች አንዱ ነው፡፡ በጣም ቀላልና በተመጣጣኝ ዋጋ ሊቀርቡ የሚችሉ መኪኖችን የሚሠሩ አምራቾች አሉ፡፡ ውድ ተሽከርካሪዎችንም የሚያመርቱ አሉ፡፡ እዚህ ባለው ገበያ የእኛ ዓላማ ለበርካታ ደንበኞች የሚስማሙ ተሽከርካሪዎችን ማቅረብ ነው፡፡ ለዚህም ነው አነስተኛ፣ መካከለኛና ትልልቅ ተሽከርካሪዎችን ለማቅረብ የምንጥረው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ጥሩ ዋጋ ያላቸውን ነው የምናመጣው፡፡ በፎርድ ኮርፖሬሽን እንደ መመርያ የምንጠቀምባቸው ሦስት የኮርፖሬት ምሰሶዎች አሉን፡፡ አንዱ ጠንካራ ቢዝነስ ነው፡፡ ሁለተኛው ጥሩ ምርት ሲሆን ሦስተኛው ደግሞ ሕግ ነው፡፡ ለደንበኞች በሚሆኑ ምርቶች ላይ አራት መርሆዎችን እንከተላለን፡፡ ጥራት፣ አረንጓዴነት፣ ደኅንነትና ብልኃት የሚባሉ መለያዎች አሉን፡፡ በእነዚህ መርሆዎች እየታገዝን ኢንዱስትሪውን እንመራለን፡፡ ስለዚህ በአረንጓዴያማነት መርህ መሠረት ነዳጅ ቆጣቢ ተሽከርካሪዎችን እያመረትን ነው፡፡ በእያንዳንዱ ተናጠል ምርታችን ላይ ነዳጅ ቆጣቢነትን መተግበር እንፈልጋለን፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባለው ሁኔታ ይኼ ምናልባት ከባድ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼውም ከነዳጅ ጥራት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የነዳጁ ጥራት ችግር ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ሞተሮችን ማምጣት አላስቻለንም፡፡ መንግሥት ተፈላጊውን የነዳጅ ጥራት ለማምጣት እንደሚሠራ እምነት አለን፡፡ ሆኖም አሁን ከመንግሥት ጋር በዕቅዶቻቸው ዙሪያ እየተነጋገርን ነው፡፡ ከፍተኛ ጥራት ያለው ነዳጅ ቢመጣ፣ ውስብስብና ከፍተኛ ብቃት ያላቸው ሞተሮች የተገጠሙላቸው ተሽከርካሪዎችን ማስገባት እንችል ነበር፡፡ የምንጠቀመው ቴክኖሎጂ በናፍጣ የሚሠሩ ሞተሮችን በመጠቀም አዲሱን ሬንጀር ሞዴል መኪና 2.2. ሊትርና 3.2 ሊትር ናፍጣ ሞተር ያለው ነው፡፡ ይህንን መኪና ለገበያ እያቀረብን ነው፡፡ በፔትሮሊየም የሚሠሩ ሞተሮች የተገጠመላቸው መኪኖችም አሉን፡፡ እነዚህም ነዳጅ በመቆጠብ በጣም የታወቁ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ግን እዚህ ማምጣት አንችልም፡፡ ግን ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ሆኖም ግን እኛ የራሳችን፣ ተቀናቃኞቻችንም የየራሳቸው ቦታ ያላቸው ይመስለኛል፡፡ ደንበኞች የሚፈልጉትን ነገር እያቀረብን ነው፡፡ ትልቅ ጥራት ያለው፣ ጥሩ ምርት፣ ድኅረ ሽያጭ በማከናወን ተወዳዳሪነታችንን እያስጠበቅን ነው፡፡
ጥያቄ፡- በአፍሪካ ትልቁ ገበያችሁ የት ነው? የማምረቻ ፋብሪካችሁ የሚገኘው በደቡብ አፍሪካ ብቻ ነው ማለት ነው?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ከአፍሪካ ትልቁ ገበያችን ደቡብ አፍሪካ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ ሆኖናል፡፡ የመጀመሪያውን ‹‹ሞዴል ቲ›› የተባለ መኪና የሸጥነው እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 1904 ነበር፡፡ ፎርድ ኩባንያ የተመሠረተው ግን እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 1903 ነበር፡፡ የመጀመሪያው ማምረቻ የተገነባው እ.ኤ.አ. በ1923 በመሆኑ፣ ላለፉት 91 ዓመታት በደቡብ አፍሪካ ስናመርት ቆይተናል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ለረጅም ጊዜ ኖረናል፡፡ እዚያ በዓመት እስከ 70,000 መኪኖችን እንሸጣለን፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ በጠቅላላው በዓመት 2,000 እንሸጣለን፡፡ ከመካከለኛው ምሥራቅ ሳዑዲ ዓረቢያ ትልቁ ገበያችን ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ሁለት የማምረቻ ይዞታዎች አሉን፡፡ አንዱ ሬንጀር መኪና የሚመረትበት ሲሆን፣ ለ148 አገሮች ኤክስፖርት ይደረጋል፡፡ ገበያው ከአፍሪካ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ያለውን ያካትታል፡፡ እርግጥ ኢራን በአሜሪካ በተጣለባት ማዕቀብ ምክንያት ወደዚያ አንልክም፡፡ ሁሉም የምራብና የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ሬንጀር የተባለውን የፎርድ መኪና ይገዛሉ፡፡ በአርጀንቲና የሬንጀር ፋብሪካ ስላለ የላቲን አሜሪካ ገበያን ይሸፍናል፡፡ በታይላንድም ተመሳሳይ ፋብሪካ ስላለ፣ አዝያን የተባለውን የንግድ ግሩፕን ይሸፍናል፡፡
በፕሪቶሪያ የመኪና መምረቻው ሲገኝ፣ በፖርት ኤሊዛቤት ከተማ ደግሞ የመኪና ሞተሮችን የሚያመርተው ፋብሪካ አለን፡፡ ፑማ የተባለውን የናፍጣ ሞተር ያመርታል፡፡ ስለዚህ በደቡብ አፍሪካ ትልቁ ማምረቻ አለን፡፡ ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ስላለው አቅም እያየን ነው፡፡ ናይጄሪያ ውስጥ ያሉ ተወዳዳሪዎቻችን አዳዲስ ማምረቻዎችን ለመገንባት ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በከሰሐራ በታች የአፍሪካ አገሮች ላይ ጥናት ከማድረግ በቀር እውነቱን ለመናገር ምንም የወሰንነው ነገር የለም፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ ከመወሰናችን በፊት በደንብ ማጥናት እንፈልጋለን፡፡ ቀድመን ላንመጣ እንችላለን፣ ስንመጣ ግን ከሰፊ መሠረተ ልማት ጋር ነው፡፡ አውቶሞቲቭ ማምረቻ ከሚሰጣቸው ጥቅሞች አንዱ በተዘዋዋሪ የሚፈጥራቸው የሥራ ዕድሎችና መሠረተ ልማቶች ናቸው፡፡ የአቅርቦት መሠረቱ ዋናው የማምረቻ ፋብሪካ ትልቅ ጠቀሜታ ነው፡፡ መቶ በመቶ የመኪና አካላትን ከውጭ በማስመጣት ላይ የተመሠረታችሁ ከሆነ፣ ማምረቻ ፋብሪካ ሊያመጣ የሚችለውን ጥቅም እያጣችሁ ነው ማለት ነው፡፡ መንግሥት ትክክለኛውን ፖሊሲ በማውጣት ለዘርፉ እንዲያውል እየመከርን ነው፡፡ አቅራቢዎች የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው ለማስቻልም እንሞክራለን፡፡
ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ የመገጣጠሚያ ፋብሪካ የመገንባት ሐሳብ አላችሁ? 
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- እንዳልኩት በኢትዮጵያም ሆነ ከደቡብ አፍሪካ ውጪ በመገጣጠሚያ ዘርፍ  ኢንቨስት ለማድረግ ምንም ዓይነት ዕቅድ የለንም፡፡ በደቡብ አፍሪካ ያለንን ድርሻ ማስፋፋት እንፈልጋለን፡፡
ጥያቄ፡- የፎርድ መምጣት ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚጨምረው እሴት ምንድነው?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ፎርድ ለኢትዮጵያ ምን ያመጣል? ለሚለው የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚዘውሩት መሣሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን መሣሪያዎች ተጠቅመው ሰዎች ገበያ የሚያወጡ ነገሮችን ያመርታሉ፡፡ እነዚህ መሣሪያዎች ኤሌክትሪክ፣ መንገዶች፣ ትምህርትና ያለጥርጥር ደግሞ እንቅስቃሴ ናቸው፡፡ ሬስ ኢንጂነሪንግ ለምሳሌ የፎርድ መኪኖችን ብቻ ሳይሆን የካተር ፒላር ምርቶች የሆኑ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችን ያቀርባል፡፡ ከእነሱ ጋር መሥራታችን መሠረተ ልማት ላይ ብቻ ሳይሆን የንግድ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ስለሚያስችለን እንደሰታለን፡፡ እዚህ የምንሸጣቸው መኪኖች ለንግድ ዓላማና ምርት ለማከፋፈል ተግባር ሲውሉ እያየን ነው፡፡ እንደ አውቶሞቲቭ አቅራቢ ኩባንያ፣ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው ጅረት ውስጥ እንገኛለን ብለን እናምናለን፡፡
ጥያቄ፡- አብዛኛው የኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ቢዝነስ ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች የተሞላ ነው፡፡ ይህ መሆኑ እንደ ፎርድ ላሉ ኩባንያዎች ምን ማለት ነው? ይኼ በመሆኑ ገበያው ውስጥ ለመግባት ሲታሰብ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወይም እንደ ፈተና ሊታይ የሚችልበት ምክንያት ምንድነው?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ምርታችንን ከሸጥንበት ቀን በኋላ መኪናው ያገለገለ መሆኑ ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡ ስለዚህ ያገለገሉ መኪኖች የሚበዙበት ኢኮኖሚና ኢንዱስትሪን እንደግፋለን፡፡ በዓለም ላይ ላገለገሉ መኪኖች ማረጋገጫ የምንሰጥባቸው በርካታ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ እነዚህን ፕሮግራሞች ወደ ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የማምጣት ስትራቴጂ አለን፡፡ ሬስ ኢንጂነሪንግ ሁለት የዚህ መሰል ተሸከርካሪዎች የሚስተናገዱበት ማዕከል እየገነባ መሆኑ አስደስቶናል፡፡ የየትኛውም ኩባንያ ሥሪት የሆኑ መኪኖች ቀላል ጥገና የሚያገኙባቸው ናቸው፡፡ ያገለገሉ መኪኖች ኢንዱስትሪ የአጋጅነቱን ያህል ጥሩ የሚባሉ አጋጣሚዎችን የሚፈጥር ነው ማለት ይቻላል፡፡ መንግሥት በኢንዱስትሪ ፖሊሲው አማካይነት አማራጭ መፍትሔ ካገኘና የትኛውን ዓይነት ተሽከርካሪ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት እንደሚቻል፣ ለምን ዓይነት ተግባር የሚውሉ መሆን እንዳለባቸው ውሳኔ ካሳለፈ፣ እኔ በእነሱ ቦታ ሆኜ ለመናገር ሳይሆን አሁን ግን  የትኛውም ዓይነት ያገለገለና አዲስ መኪና አቅርቦት ላይ እንሳተፋለን፡፡
ጥያቄ፡- ጥቂት የቻይናና የመንግሥት ድርጅቶች የመገጣጠም ሥራ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡ ይኼ ለእናንተ ምን ማለት ነው? በመጪዎቹ አምስት ወይም አሥር ዓመታት ውስጥ የቻይና አዳዲስ መኪኖች የኢትዮጵያን ገበያ፣ አልፎም የጎረቤት አገሮችን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ የሚል ግምትም አለ፡፡
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- በቻይና ከሚሸጠው መኪና ውስጥ ምን ያህል እጁ እዚያው ቻይና የተሠራ ነው የሚለውን አኃዝ ብንመለከት ብዙ የሚባል አይደለም፡፡ ይልቁንም በርካታ የውጭ ምርቶች ናቸው የሚሸጡት፡፡ ደንበኞች አማራጭ ማግኘታቸው ተገቢ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ውድድርንም እቀበላለሁ፡፡ እኔ ግን ሰዎች ፎርድን እንዲመርጡ ነው የምፈልገው፡፡ ጥሩ እሴት ያለው በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ቻይኖች የት ይደርሳሉ፣ ኮሪያዎች ይህንን ይሠራሉ በሚለው ነገር ላይ አስተያየት መስጠት አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም እነሱ የራሳቸው የቢዝነስ ዕቅድ አላቸው፡፡ እኔን የሚያሳስበኝ የራሴ የቢዝነስ ዕቅድ ነው፡፡
ጥያቄ፡- በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ በዓመት ምን ያህል መኪኖችን ትሸጣላችሁ?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- በሥሌታችን መሠረት የገበያውን ዘጠኝና አሥር በመቶ ድርሻ እንሸጣለን፡፡ ይህንን በሚገባ ለማሳየት በአውሮፓ ዘጠኝ በመቶ፣ በደቡብ አፍሪካ 13 በመቶ፣ በቻይና አራት በመቶ፣ በአሜሪካ 15 በመቶ የገበያ ድርሻ አለን፡፡ ስለዚህ አሥር በመቶ ጥሩ አኃዝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ከዓለም ገበያ ድርሻችን ከአማካይ በላይ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ ያላችሁ የገበያ ድርሻ እስከ አሥር ከበመቶ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በገንዘብ ደረጃ ሲገለጽ ምን ያህል ይሆናል?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- የግል ኩባንያ በመሆናችን የሽያጭ መጠናችንን ይፋ አናደርግም፡፡ እርግጥ የእኛም ሳይሆን የሬስ ኢንጂነሪንግ ዓመታዊ ሽያጭ ነው፡፡ ዓመታዊ ሽያጫችንን በቀጣና ደረጃ ነው ይፋ የምናደርገው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ሁለተኛው ሩብ ዓመት የነበረን ዓመታዊ ሽያጭ 34 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡
ጥያቄ፡- የአገር ውስጥ ወኪሎች ከውጭ ምንዛሪ ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ኩባንያዎ ምን ይላል? የምንዛሪ እጥረቱ በፎርድ ኩባንያ ላይ ተፅዕኖ አድርሶበታል?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ችግሩ ፎርድ ኩባንያን ለይቶ ተፅዕኖ የሚፈጥርበት አይደለም፡፡ የትኛውንም ዕቃ የሚያስመጣ ሁሉ ተፅዕኖው ያርፍበታል፡፡ የመንግሥት ሁኔታ ይገባኛል፡፡ የንግድ ሚዛኑን ማስጠበቅ አለባቸው፡፡ ከኢኮኖሚ ፖሊሲው ጋር የሚጣጣም የውጭ ምንዛሪና ዋጋ መኖሩን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይኼንን እረዳለሁ፡፡ ከተወያየንባቸው ጉዳዮች አንዱ ይኼ ሲሆን፣ መንግሥት የንግድ ሚዛኑን እንዴት ሊያስጠብቅ ይችላል በሚለው ላይ ሐሳባችንን አቅርበናል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ትልቅ ፋብሪካ አለን፡፡ ለዚህ ፋብሪካ የሚያቀርቡ 300 ድርጅቶችም አሉን፡፡ ከእነዚህ አንዱን ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲያመጣ ለማድረግ ይቻል እንደሆነ እያሰብን ነው፡፡ ምሳሌ ነው፡፡ አላውቅም፡፡ ገና በሐሳብ ደረጃ ነው የተወያየንበት፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ መንግሥትን ማገዝና የሚሠሩትን ሥራ መሥራት እንዲችሉ መርዳት ይቻል ይሆናል፡፡ የውጭ ምንዛሪው ነገር አገሪቱ ካላት ከወጪ ንግድ ይልቅ ገቢ ንግድ ላይ ያተኮረ የንግድ ሚዛን የሚመነጭ ነው፡፡ ፎርድ ወይም ሌሎች ኩባንያዎች ብቻቸውን ሊፈቱት አይችሉም፡፡ ትንንሹ ነገር ግን ሊያግዝ ይችላል፡፡ የምንዛሪው እጥረት ግን ጎታች ነው፡፡ በወቅቱ ማግኘት አለመቻል፣ በውጭ ምንዛሪ ላይ የተመሠረተ ግብይት ለማድረግ ፈቃድ ማግኘት፣ የታዘዘውን መኪና ማስገባት ሁሉ ከባድ ነው፡፡ እያማረርኩ አይደለም፡፡ ችግሩን እረዳለሁ፡፡ መንግሥት የተለያዩ ፖሊሲዎችን ሚዛን ለማስጠበቅ እንደሚጥር እረዳለሁ፡፡ ልንረዳቸው የምንችልባቸውን መንገዶች ለማየት እንሞክራለን፡፡
ጥያቄ፡- ፎርድ ፋውንዴሽን ከአራት አሥርታት በፊት በአፍሪካ ግብርና ላይ ለውጥ ያመጣል በተለባው አረንጓዴ አብዮት ዘመቻ ላይ ድጋፍ አድርጎ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ዓላማ ያለው አዲሱ አፍሪካ አረንጓዴ አብዮትም ጉባዔውን እዚህ አካሂዷል፡፡ እንዲህ ያሉ መዋቅሮችን አሁንም ትደግፋላችሁ? 
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- የፎርድ ፈንድ ኩባንያው በአፍሪካ ከሚያካሂደው ኢንቨስትመንት አኳያ ገለልተኛ ነው፡፡ የቀጣና ጽሕፈት ቤት የመክፈት አንዱ ጥቅሙም በምንሠራበት አካባቢ ያሉ ማኅበረሰቦችን ልንደግፍ የምንችልባቸውን መንገዶች በማየት ከፎርድ ፈንድ ጋር እንነጋገራለን፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ እንዲህ ብዬ ልናገረው የምችለው ነገር ይዤ ባልመጣም፣ ድጋፍ ይሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ክፍተቶችን እናያለን፡፡ ከምንሠራበት አካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ጥሩ ማኅበራዊ አጋርነት መመሥረትን እንፈልጋለን፡፡ ሬስ ኢንጂነሪንግም በዚህ አኳኋን ጥሩ ይሠራል፡፡ የሚደግፋቸው ትምህርት ቤቶች አሉ፡፡ የአዕምሮ ዕድገት ውሱንነት ላለባቸው (ኦቲዝም) ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የግንባታና የጥገና ዕቃዎችን ይለግሳል፡፡ ለመንገድ፣ ለሆስፒታልና ለትምህርት ቤት መገንቢያ የሚረዱ መሣሪያዎችን ይረዳል፡፡ በዚህ ተግባር በጣም እንኮራለን፡፡
ጥያቄ፡- ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ለኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነቱ ፎርድ ምን አስቧል?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ከተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና በጎ አድራጎት ተቋማት ጋር አጋር በመሆን እንደየአገሩ ሁኔታ በምንንቀሳቀስባቸው፣ ምርታችንን በምናቀርብባቸው፣ የጥገናና ሌሎች ሥራዎችን በምናከናውንባቸው አካባቢ የሚገኙ ማኅበረሰቦች ያሏቸውን ፍላጎቶች በማየት ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ አንዳንዶቹ ንፁህ ውኃ፣ አንዳንዶቹ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ሌሎቹ ትምህርት፣ የሕፃናት ክብካቤ ወይም ምግብ የሚፈልጉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በማኅበረሰቡ ፍላጎት ላይ በመመሥረትና ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለንን ነገር በማጥናት ድጋፍ እንሰጣለን፡፡ እኛ የምግብ ባንክ ወይም የትምህርት ተቋማት ሳንሆን መኪና አምራቾች መሆናችንን መርሳት የለብንም፡፡ ለዚህም ነው በዚህ መስክ ከተሰማሩ ጋር አጋር በመሆን ገንዘብ፣ መኪና ወይም ሌላ ቁሳቁስ በመስጠት ድጋፍ የምናደርገው፡፡ እንደየሁኔታው የተለያየ ነው፡፡ ከኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነታችን አኳያ አንድ ነገር ላይ ያጠነጠነ የፓን አፍሪካ ስትራቴጂ የለንም፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ኃላፊነታችንን በዓለም ላይ በአግባቡ የሚያራምድ ትልቅ ተቋም አለን፡፡ ለሥራችንና ለምንሰጠው ድጋፍ ተገቢውን ውጤት እያገኘንበት ነው፡፡
ጥያቄ፡- ከሰሐራ በታች የሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ገበያ አኳያ የኢትዮጵያን ገበያ እንዴት ይመለከቱታል? የገበያ ድርሻውስ ምን ይመስላል?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- በዓለም ጥሩ የሚባለውን ምርት ስለምናቀርብ የኢትዮጵያ ገበያ ጥሩ ነው እንላለን፡፡ ዕድገቱ ተፈጥሯዊ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላት በመሆኑ፣ ለዚህ ዘርፍ የሚሆኑ ሬንጀር ፒካፕ መኪኖች አሉን፡፡ ትልልቅ ጭነት መጫን የሚችሉ፣ ነዳጅ የሚቆጥቡና በዋጋ ደረጃም ተመጣጣኝ በመሆናቸው ለኢትዮጵያ ግብርና ተስማሚ መሆናቸውን አይተናል፡፡ በርከት ያሉ የሬንጀር ፒካፕ መኪኖች እዚህ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውም ጥሩ ድጋፍ ለመስጠታቸው ምስክር ነው፡፡ የሥራ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ ለንግድ፣ ለአነስተኛ ቢዝነሶችና ለገበሬዎች ጥሩ ጥቅም የሚሰጡ ናቸው፡፡ ምርቶቻቸውንና የዘር ዓይነቶችን ለማጓጓዝ ምቹ መሆናቸውንና ሌሎች ጥቅሞችን ልንዘረዝር እንችላለን፡፡ ሬስ እንጂነሪንግ የግብርና ማሽነሪዎችንና ልዩ ልዩ መሣሪያዎችን የሚያመጡ በመሆናቸው የሁለታችን ጥምረት መልካም እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በሰፋፊ የልማት ሥራዎች ላይ ትገኛለች፡፡ ለአፍሪካና ለመካከለኛው ምሥራቅ 25 አዳዲስ ምርቶችን ይፋ ልታደርጉ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ እንቅስቃሴ አኳያ እነዚህ ምርቶች ምን ትርጉም ይኖራቸዋል?
ጄፍሪ ኒሜዝ፡- ከ25 አዳዲስ ምርቶች  በተለይ 17ቱ ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገሮች የሚውሉ ናቸው፡፡ ከእያንዳንዱ ገበያ ፍላጎት በመነሳት ምቹ አቀራረብ እንከተላለን፡፡ በአሁኑ ወቅት ምርቶቻችንን ከምንገኝባቸው ገበያዎች ፍላጎት አኳያ በመነሳት ለማምረት እያሰብን ነው፡፡ የቀጣና ጽሕፈት ቤት አንዱ ጥቅምም ይኼው ነው፡፡ ለምርምርና ጥናት እንዲሁም ለምህንድስና ክፍሎቻችን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነዳ መኪና ከመሬት ያለው ከፍታ እንዲስተካከል እንነግራቸዋለን፡፡ ስለዚህ አሁን የቀረቡት አዳዲስ መኪኖች ጥሩ ምሳሌ ናቸው፡፡ ምንጊዜም ደንበኞች ከሚፈልጓቸው ይዘቶች በመነሳት ምርት እናመርታለን፡፡ በጣም ውስብስብ ምርቶችን በምናቀርብባቸው ገበያዎች ላይ ጥናት እናደርጋለን፡፡ ደንበኞች ምን እንደሚፈልጉ እንጠይቃቸዋለን፡፡ ወደፊት በሚገዙት መኪና ውስጥ ምን ምን እንዲካተት እንደሚፈልጉ በመጠየቅ ጥናት እናካሂዳለን፡፡ በዳሽ ቦርድ ላይ ስልክ እያስገባን ነው፡፡ ‘አፕሌክ’ የተባለውን ዘመናዊና ታዋቂነት ያተረፈውን ሥርዓት እየገጠምን ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የሞባይል ስልኮች መኪናው ውስጥ ከተገጠሙ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን በመጫን መጠቀም የሚያስችል ነው፡፡
ስለዚህ በማሽከርከር ወቅት የስልክ ጥሪዎችን መቀበል ሳያስፈልግ፣ መኪና ውስጥ በማስቀመጥ ብቻ ግንኙነት ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህ ቴክኖሎጂ በአፍሪካ የሚተገበር ይሆናል፡፡ ለኢትዮጵያም በምናቀርባቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ተገጥሞ ይመጣል የሚል ሐሳብ አለን፡፡ ለአሁኑ ግን ከወኪሎች ጋር ደንበኞች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች እየተነጋገርን ነው፡፡ ወደፊት ምን ይፈልጋሉ በሚለው ላይ ጥናት እያደረግን ነው፡፡ ፎርድ ኩባንያ ምን ዓይነት ጥቅም ለኢትዮጵያ ሊያመጣ ይችላል ለሚለው የተወሰኑ ነገሮችን ማየት አለብን፡፡ እንደ ፎርድ ያሉ የኮርፖሬት እሴቶቻችን ጠንካሮች ናቸው፡፡ ከማኅብረሰቡ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አለን፡፡ መንግሥት አገሪቱን መውሰድ በሚፈልግበት አቅጣጫ በኩል ድጋፍ ለማድረግም ፍላጎት አለን፡፡ በተደጋጋሚ ሚኒስትሮችን እያነጋገርን ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በአገሪቱ ውስጥ አስፈላጊ ስለሆነው ነገር የሚያስቡትን እናወያያቸዋለን፡፡ ወደ አገሪቱ ምን ማምጣት እንደምንችል እንመክራለን፡፡ 

No comments:

Post a Comment