Tuesday, September 9, 2014

ለከተማ ባቡር የሚያገለግሉ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች ጥራት በአማካሪ ድርጅቱና በኢንሳ ተመረመሩ

የአዲስ አበባ ቀላል የከተማ ባቡር ፕሮጀክት ሥራ ሲጀምር አገልግሎት ላይ የሚውሉ የኮሙዩኒኬሽንና የሲግናሊንግ መሣሪያዎች የምርት ጥራት ደረጃ፣ ከአማካሪ ድርጅቱና ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተወጣጡ ባለሙያዎች ምርመራ ተካሄደባቸው፡፡
ከመረጃ መረብና ደኅንነት ኤጀንሲና ከኢትዮ ቴሌኮም የባቡር መስመር ዝርጋታውን ኮንትራት የወሰደው አማካሪ ድርጅት ስዌድሮድ የተወጣጡ ባለሙያዎች፣ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎቹ የሚመረቱበት ቻይና በመሄድ የጥራት ደረጃቸውን በመመርመር ጥራታቸውን ማረጋገጣቸውን፣ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመረጃ መረብና ደኅንነት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች ደኅንነትና  የጥራት ደረጃ የመመርመር ኃላፊነት የወሰደው፣ መሣሪያዎቹ ከአገር ደኅንነት አንፃር ብቁ መሆናቸውን ለመፈተሽ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎችን ለማምረት አጠቃላይ የባቡር ሥራ ኮንትራቱን የወሰደው የቻይናው ሲአርኢሲሲ የመረጠው ሁዋዌ የቴሌኮም ኩባንያ ነው፡፡
የባቡር ሥራ ኮንትራቱ የኢንጂነሪንግ፣ የግዢና ኮንስትራክሽንን አጠቃሎ 475 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽንና የሲግናሊንግ መሣሪያዎችን እንዲያመርቱ በተመረጡ ኩባንያዎች የአመራረጥ ሒደት ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ ታውቋል፡፡
የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎቹ የሚያገለግሉት ባቡሩ ከአንድ ጣቢያ ተነስቶ ወደ ሌላ ጣቢያ በሚጓዝበት ወቅት ያሉ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር፣ በአንድ ጣቢያ ያለውን የትራንስፖርት ፍላጎት በመመልከት ባቡር ለመመደብ፣ ባቡሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች ሙሉ እንቅስቃሴን የሚያሳዩ ካሜራዎችን ለመትከል ነው፡፡
በቁጥጥር ማዕከልና በባቡር እንቅስቃሴ መካከል የሚኖር ገመድ አልባ የመረጃ ልውውጥ የሚደረገው በእነዚህ የኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች መሆኑ ታውቋል፡፡
የሲግናሊንግ መሣሪያዎችን እንዲያመርት የተመረጠው ካስኮ የተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን፣ መሣሪያዎቹ የሚያገለግሉት ባቡሩና ተሽከርካሪ መኪኖች በሚገናኙባቸው አካባቢዎች ባቡሩ ቅድሚያ እንዲያገኝ መልዕክት እንዲያስተላልፍ እንደሆነ የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል፡፡
የተመረቱ ምርቶች በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ መግባት አለባቸው ተብሎ በተቀመጠ አቅጣጫ መሠረት፣ ምርቶቹ በአሁኑ ወቅት በመጓጓዝ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የባቡር ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ የተጠናቀቀ መሆኑን፣ ቀሪው 25 በመቶ የኮንትራቱ ጊዜ በሚጠናቀቅበት ቀሪዎቹ አምስት ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮርፖሬሽኑ ገልጿል፡፡
አንዳንድ ምንጮች ፕሮጀክቱ በተባለው ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደማይገመት እየገለጹ ቢሆንም፣ ኮርፖሬሽኑ ግን በተባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ 24 ሰዓት እየተሠራ መሆኑንና እስካሁንም ከኮንትራክተሩ የቀረበለት የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ እንደሌለ  አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment